ኮሮናቫይረስ ፡ የኦክስፎርድ-አስትራዜኔካ ክትባት በዩናይትድ ኪንግደም ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ አገኘ

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኦክስፎርድ-አስትራዜኔካ ክትባት ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ ማግኘቱ ተገልጿል። በሚቀጥለው ሰኞ ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ክትባቶች ለሰዎች መሰጠት እንደሚጀምሩ ተገልጿል።

ዩኬ የዚህን ክትባት 100 ሚሊየን ብልቃጦች ያዘዘች ሲሆን ለ50 ሚሊየን ሰዎች ይበቃል።

ከፋይዘር እና ባዮንቴክ የታዘዘው ክትባት ከኦክስፎርድ- አስትራዜኔካ ጋር ሲደመር መላውን ሕዝብ ለመከተብ ያስችላል ብለዋል የጤና ሚንስትር ጸሐፊው ማት ሃኖክ።

የዚህ ክትባት ክትባት ፈቃድ ማግኘት በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ምክንያት ጠበቅ ባል ገደብ ስር ለሆኑ በሚሊየኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ትልቅ ተስፋን ይዞ የመጣ እንደሆነ ተገልጿል።

ማክሰኞ ዕለት በዩናይትድ ኪንግደም ተጨማሪ 53 ሺ 135 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋጋጠ ሲሆን አገሪቱ በብዛት መመርመር ከጀመረች ወዲህ ይህ ከፍተኛው ቁጥር እንደሆነ ተገልጿል። በተጨማሪም 414 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው ካወቁ በ28 ቀናት ውስጥ ሕይወታቸው አልፏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በክትባቶች ዙሪያ እየታየ ያለውን ስኬት በዩኬ የሳይንስ እድገት "ትልቅ ድል" ለማስመዝገቡ ማሳያ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። አክለውም ''ከዚህ በኋላ በቻልነው ፍጥነት የቻለንውን ያክል ሰው ወደ መከተብ ነው የምንገባው'' ብለዋል።

የእንግሊዝ ዋና ሜዲካል ኦፊሰር የሆኑት ክሪስ ዊቲ በጥምረት ተገኘ ላሉት ስኬት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የክትባት ማዕከላት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ሰዎች ወደ ማዕከላቱ እየመጡ ክትባቱን እንዲወስዱ ጥሪ ማስተላለፍ ይጀምራሉ ተብሏል። ይህ ክትባት ለማስቀመጥና ለማጓጓዝ የማያስቸግር በመሆኑ የክትባቱን ስራ በእጅግ እንደሚያቀለው ተገምቷል።

በተጨማሪም በመጀመሪያ ፈቃድ ያገኘው የፋይዝ/ባዮንቴክ ክትባት ከቤልጂየም ድረስ ተጓጉዞ የሚመጣ መሆኑ የኦክስፎርድ-አስትራዜኔካ ክትባትን ተመራጭ ያደርገዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም እቅድ መሰረት በየሳምንቱ ሁለት ሚሊየን ሰዎችን ለመከተብ የታሰበ ሲሆን ሁለት አይነት ክትባቶች መኖራቸው ደግሞ ስራውን ሊያቀለው ይችላል።

በዩኬ እስካሁን 600 ሺ ሰዎች የፋይዘር/ባዮንቴክ ክትባትን አግኝተዋል። በዓለማችን የመጀመሪያውን ክትባት የወሰዱት ደግሞ ማርጋሬት ኪን የተባሉት የእድሜ ባለጸጋ ናቸው።