ኮሮናቫይረስ፡ በሩሲያ በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች መንግሥት ከገለፀው ሦስት እጥፍ ይበልጣል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የሩሲያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ታቲያና ጎሊኮቫ በዚህ የፈረንጆች ዓመት በአገሪቱ ከተከሰቱት ሞቶች 80 በመቶ ያህሉ በኮቪድ-19 ምክንያት የመጡ መሆናቸውን ተናገሩ።
ይህም ማለት ከዚህ ቀደም መንግሥት በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሞተውብኛል በማለት ሪፖረት ካደረገው ቁጥር ሦስት እጥፍ ይሆናል ማለት ነው።
ሩሲያ 55,827 ዜጎቿ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሞተዋል በማለት ሪፖርት ያደረገች ሲሆን፤ የአሁኑ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መረጃ ይህንን ቁጥር ወደ 186,000 ከፍ ያደርገዋል ተብሏል።
ጎሊኮቫ በ2020 የመጀመሪያዎቹ 11 ወራት በአገሪቱ ያጋጠመው የሟቾች ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ13.8 በመቶ ይበልጣል ብለዋል።
የሩሲያ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን በበኩሉ በዚህ ዓመት ተጨማሪ 229,700 ዜጎች መሞታቸውን አስታውቋል።
ስለዚህ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ መሰረት 186,057 ሞቶች በቀጥታ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ ናቸው ማለት ነው።
ይህ ቁጥር የሩሲያ የስታትስቲክስ ባለሥልጣን ይፋ አድርጎት ከነበረው ቁጥር የበለጠ ነው ተብሏል።
በዓለም ላይ እስካሁን ድረስ በከፍተኛ ሁኔታ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ዜጎቻቸውን በሞት መነጠቃቸውን ሪፖርት ያደረጉት አሜሪካ እና ብራዚል ናቸው።
ሩሲያ በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎችን ቁጥርን የምታሰላው የአስከሬን ምርመራ ተደርጎ የሞታቸው መንስዔ በትክክል ኮሮናቫይረስ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ነው።
ይሁን እንጂ ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ ሌሎች ሞቶች በኮሮናቫይረስ ባስከተለው ተያያዥ ምክንያት የሞቱ በሚል አይካተትም ነበር።
ነገር ግን በኅዳር ወር ብቻ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ ሞቶች በሩሲያ ከፍተኛ መሆናቸውን የአገሪቱ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን መረጃ ያሳያል።
በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ ባለፈው ወር የተከሰቱ ሞቶች ከአስሩ አንዱ ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዘ ነበር ተብሏል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጎሊኮቫ መንግሥታቸው በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተከሰቱ ሞቶችን ቁጥር አልደበቀም ሲሉ ፍርጥም ብለው ተከራክረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኅዳር እና ታህሣስ ወራት አገሪቱ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተጠቃችባቸው ጊዜያት ሁሉ የከፉት ነበሩ ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የአገራቸውን የጤና ሥርዓት ያንቆለጳጰሱ ቢሆንም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሆስፒታሎች ግን በኮቪድ-19 ምክንያት ታመው እርዳታ በሚሹ ሰዎች ተጨናንቀዋል ተብሏል።
ሩሲያ ምንም እንኳ በአውሮፓ ኅብረት የመድኃኒቶች ኤጀንሲ ባይረጋገጥም ስፑትኒክ 5 በማለት የሰየመችውን የኮሮናቫይረስ ክትባት አምርታ ለዜጎቿ መከተብ እንዲሁም ወደ ቤላሩስ፣ አርጀንቲናና ሃንጋሪ መላክ ጀምራለች።
በቤላሩስ ማክሰኞ እለት ክትባቱ መሰጠት የተጀመረ ሲሆን በሩሲያ ደግሞ በአጠቃላይ 700,000 ክትባቶች ተሰራጭተዋል ተብሏል።












