የቻይናን ሰንደቅ አላማ ተሳድቧል የተባለው የ19 ዓመቱ 'አክቲቪስት' ታሠረ

ቶኒ ቹንግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ተማሪው የሆንግ ኮንግ ነዋሪ ቶኒ ቹንግ የቻይና ሰንደቅ አላማ ላይ በመሳለቁ ምክንያት የአራት ወራት እሥር ተፈረደበት።

ተማሪው ተሟጋች [አክቲቪስት] ባለፈው ግንቦት በነበረ ተቃውሞ ላይ ነው የቻይና ሰንደቅ አላማ የዘለፈው ተብሏል።

የ19 ዓመቱ የሆንግ ኮንግ ወጣት እንደውም የሦስት ዓመት እሥር ይጠብቀው ነበር።

የቻይና ፍርድ ቤት ቹንግ የቻይናን ሰንደቅ አላማ ከዘንጉ አውርዷል፤ መሰቀያ ዘንጉን ሰብሯል፤ አልፎም ሰንደቅ አላማው ወደ ሰማይ ወርሯል ሲል ከስሶታል።

ወጣቱ ቹንግ ብሔራዊ ደኅንነትን አደጋ ላይ በመጣል ክስ ሌለ ችሎት እየተከታተለ ነበር።

የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች ቻይና አዲስ ያወጣችውን መመሪያ በመቃወም ለወራት ተቃውሞ በማሰማት ላይ ናቸው።

መመሪያው ሆንግ ኮንግ ውስጥ ወንጀለኛ ሆኖ የተገኘ ሰው ለቻይና ተላልፎ እንዲሰጥ ያዛል።

ስቱደንትሎካሊዝም የተሰኘው የነፃነት ቡድን አባል የሆነው ወጣት ሰንደቅ አላማ ከማንቋሸሽ አልፎ ሕጋዊ ባልሆነ ሰልፍ ላይ ተሳትፏል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

ቻይና በሆንግ ኮንግ የዴሞክራሲ ሰልፈኞች ላይ እርምጃ እየወሰደች ነው። ይህ ደግሞ በርካቶች ሃገሪቱን ጥለው እንዲወጡ አስገድዷቸዋል።

ወጣቱ ቹንግ ሰንደቅ አላማ በማንቋሸሽ የተፈረደበትን ፍርድ እየተከታተለ በብሔራዊ ደህንነት የቀረበበትን ክስ ደግሞ ይከታተላል።

ቻይና ባለፈው ሐምሌ ነው ከውጭ ኃይሎች ጋር አብረዋል፣ ለመገንጠል አስበዋል እንዲሁም የአገሪቱን ሰላም አደፍርሰዋል ያለቻቸውን ሰዎች የከሰሰችው።

ቻይና ሆንግ ኮንግ ላይ የጫነችው አዲሱ መመሪያ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትችት እንዲሰነዘርባት አድርጓል።

ሕጉ ከእንግሊዝ አገዛዝ በፈረንጆቹ 1997 ነፃ የወጣችውን ሆንግ ኮንግ ራስ ገዝ አስተዳደር የሚንቅ ነው ተብሏል።

የቻይና መንግሥት የቀረቡበትን ትችቶች አጣጥሏል።

ቻይና ሕጉ በ2019 በሆንግ ኮንግ የታየውን ዴሞክራሲን በመደገፍ የሚደረግ ተቃውሞ ለማስቀረት ይበጃል ትላለች።

ወጣቱ ቾንግ ባለፈው ጥቅምት ነው ሲቪል በለበሱ ፖሊሶች ከዩናይትድ ስቴትስ ቆንስላ አቅራቢያ ታፍኖ የተወሰደው።

መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው 'ፍሬንድስ ኦፍ ሆንግ ኮንግ' የተሰኘው ተቋም እንደሚለው ቹንግ ወደ አሜሪካ ቆንስላ ገብቶ ጥገኝነት ለመጠየቅ አስቦ ነበር።

ተሟጋቹ ከላይ ከቀረቡበት ክሶች ባለፈ በሕገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር ሌላ ክስ ይጠብቀዋል።

ከወጣቱ በተጨማሪ ሌለች 10 የሆንግ ኮንግ አክቲቪስቶች በጀልባ ወደ ታይዋን ሊያመልጡ ሲሉ ተይዘው በተመሳሳይ ችሎት ክሳቸው ታይቷል።

ብዙዎች እሥር ይጠብቃቸዋል ተብሏል።