ትግራይ ፡ "አገሬ ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ናት፤ ተጨንቄያለሁ" ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢትዮጵያዊው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው ተናገሩ።
ዳይሬክተሩ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት የቀሩትን የፈረንጆች 2020 በተመለከተ ባደረጉት ንግግር ላይ "ኮቪድ አልበቃ ብሎ እኔ ደግሞ የግል ህመም አለብኝ። ስለ አገሬ እጨነቃለሁ" ብለዋል።
"ከኮቪድ-19 በተጨማሪ 2020 ከባድ የሆነብኝ አገሬ ችግር ውስጥ ስለሆነች ነው" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ፤ በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ ባደረጉት ንግግር፤ "አገሬ ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ናት። በእናት አገሬ ኢትዮጵያ፣ በትውልድ ቀዬዬ ትግራይ እየተካሄደ ያለው አስከፊ ጦርነት ያስጨንቀኛል" ሲሉ ተደምጠዋል።
አያይዘውም ታናሽ ወንድማቸውን ጨምሮ ሌሎች የቤተሰብ አባሎች የት እንዳሉ እንደማያውቁ ዶ/ር ቴድሮስ ገልጸዋል።
"የግንኙነት መስመሮች ስለተቋረጡ ታናሽ ወንድሜንና ዘመዶቼን አላገኘኋቸውም። ወንድሜና ዘመዶቼ የማኅበረሰቡ አካል ናቸው። ስለ ታናሽ ወንድሜና ስለ ዘመዶቼ ብቻ ልጨነቅ አልችልም። የምጨነቀው ስለመላው አገሪቱ ነው" ብለዋል።
በአጠቃላይ በመጠናቀቅ ላይ ያለው የፈረንረጆቹ 2020 ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ለሁሉም ሰው አስከፊና አሳዛኝ ዓመት እንደሆነ ጠቅሰው፤ እሳቸው ደግሞ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ተጨምሮ ዓመቱን ከባድ እንዳደረገባቸው አክለዋል።
ዶክተር ቴድሮስ በዓመቱ ውስጥ የድርጅታቸው ዋነኛ ተግባር ስለነበረው የኮረናቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ ስላጋጠሙ ችግሮች፣ ቫይረሱን በተመለከተ ስለተደረጉ ጥረቶችና አሁን ስለተተደረሰባት ውጤት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በትግራይ ክልል በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊትና በህወሓት ኃይሎች መካከል ግጭት በሚካሄድበት ጊዜ ህወሓትን ለመደገፍ ጥረት አድርገዋል በሚል በከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ክስ ቀርቦባቸው ነበር።
የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በወቅቱ እንዳመለከቱት ዶክተር ቴድሮስ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ገብቶ የነበረውን ህወሓት በመደገፍ "አንዳንድ በሮችን ማንኳኳታቸውን" በመግለጽ ከሰዋቸው ነበር።
ዶ/ር ቴድሮስ ለቀረበባቸው ለዚህ ክስ በወቅቱ በትዊተር ገጻቸው ላይ በሰጡት ምላሽ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው ነገር ልባቸውን እንደተሰበረ አመልከተው "በዚህ ውስጥ አንድ ወገንን እንደደገፍኩ የሚገልጹ ዘገባዎች ሲወጡ ቆይተዋል። ነገር ግን ይህ እውነት አይደለም" ብለዋል።
ጨምረውም "እኔ የምደግፈው አንድ ወገን ቢኖር ሠላም የሚመጣበትን መንገድ ብቻ ነው" ሲሉ ለሠላም ያላቸውን ድጋፍ ገልጸው ነበር።













