ኮሮናቫይረስ፡ ስርጭቱ እንደ አዲስ ያገረሸባት ደቡብ አፍሪካ ገደቦችን አስቀመጠች

የፎቶው ባለመብት, EPA
በደቡብ አፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ከአንድ ሚሊየን መሻገራቸውን ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ አዲስ ጠበቅ ያሉ ገደቦችን ማስተላለፋቸው ተሰምቷል።
ቤት ውስጥና ከቤት ውጪ ሰዎች ሰብሰብ ማለት አይችሉም ተብሏል፣ ከመሸ በኋላ እንቅቃሴ ማድረግም የተከለከለ ሲሆን ማንኛውም አይነት የአልኮል መጠጥም ቢሆን አይሸጥም።
ፕሬዝዳንት ራማፎሳ በቴሌቪዥን መስኮት ባስተላለፉት መልዕክት ላይ ደቡብ አፍሪካ በወረርሽኙ ምክንያት አስፈሪና አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መድረሷን ጠቅሰው አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ግድ አንዳለ አስረድተዋል።
በቅርብ ቀናት የአገሪቱ ባለስልጣናት በፍጥነት እየተዛመተ የሚገኝ አዲስ አይነት ቫይረስ መኖሩን ማረጋገጣቸው ይታወሳል።
አንዳንድ ሆስፒታሎችና የሕክምና ማዕከላት በርካታ ሰዎችን ተቀብለው እያስተናዱ እንደሆነና የግብአት እጥረት እያጋጠማቸው ስለመሆኑም እየገለጹ ነው።
ይህንን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ ባስተላለፉት መልዕክት ''501.V2 የሚባል አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተገኝቷል። በአሁኑ ሰአት ደግሞ በርካታ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ መሆኑ በጣም አሳሳቢ ያደርገዋል። የጥንቃቄ እርምጃዎቻችንን ችላ ማለታችን ነው ለዚህ ያበቃን'' ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም አዲሶቹ ጥብቅ ገደቦች ከሰኞ ምሽት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንና ቢያንስ ለሚቀጥሉት ሶስት ሳምንታት ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።
''ከቀብር ስነ ስርአት ውጪ ማንኛውም አይነት ሰዎችን የሚያሰባስብ ማህበራዊ ክንውን ተከልክለሏል፣ ሰዎች ከመሸ በኋላ መንቀሳቀስ አይችሉም፣ ሁሉም ሱቆች፣ መጠጥ ቤቶችና ምግብ ቤቶች ልክ ከምሽቱ ሁለት አሰት ላይ መዘጋት አለባቸው'' ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
የአልኮል መጠጦችን መሸጥም ቢሆን የተከለከለ ሲሆን ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረግ ግዴታ ነው ተብሏል። አለበለዚያ ደግሞ እስር እንደሚጠብቃቸው ተገልጿል።
ባሳለፍነው እሁድ ደቡብ አፍሪካ በቫይረሱ የተያዙ ከአንድ ሚሊየን ሰዎችን በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነች ሲሆን እስካሁን ድረስ 26 ሺ 735 ሰዎች በዚሁ ቫይረስ ምክንያት ሞተዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት በአማካይ 11 ሺ 700 ሰዎች በየቀኑ በኮቪድ-19 እየተያዙ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ከባለፈው ሳምንት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ የ39 በመቶ ጭማሪ አለው ተብሏል።
ለዚህ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር በዋነኛነት የተቀመጠው ምክንያት ደግሞ አዲሱ የኮሮረናቫይረስ አይነት እንደሆነ ተጠቁሟል። አዲሱ ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በሰሜናዊ ኬፕ ሲሆን በአሁኑ ሰአት በፍጥነት እየተዛመተ ነው።
ዩናይትድ ኪንግደም በዚህ አዲስ አይነት ቫይረስ ምክንያት ከደቡብ አፍሪካ የሚመጡ ተጓዦችን ማገዷን አስታውቃ ነበር። ሌላ አይነት ቫይረስ ደግሞ በዩናይትድ ኪንግደም መገኘቱም የሚታወስ ነው።












