የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በሻይ ስኒ አልኮል እንዳይሸጥ ከለከለ

ትኩስ ነገር ነው ወይስ አልኮል መጠጥ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ሚኒስትር ምግብ ቤቶች ለደንበኞቻቸው በሻይ ብርጭቆ አልኮል እንዳይቀርቡ አስጠንቅቀዋል።

ደቡብ አፍሪካ ኮሮናቫይረስ ከገባ ለሁለተኛ ጊዜ አልኮል እንዳይሸጥ ከልክላለች።

ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ሰዎች አልኮል ጠጥተው "የሚተገብሩት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር" ለኮቪድ-19 መስፋፋት ምክንያት ነው ብለዋል።

ፕሬዝደንቱ ይህን ያሉት አዲሱን መመሪያ ይፋ ባደረጉበት ወቅት ነው።

በፍጥነት እየተዛመተ ያለው አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ደቡብ አፍሪካ ገብቷል።

ራማፎሳ አዲሱ ዝርያ በደቡብ አፍሪካ በፍጥት እየተዛመተ ነው ብለዋል።

ደቡብ አፍሪካዊያን ለቀብር ካልሆነ በቀር ሰብሰብ ብለው እንዳይታዩ ታግደዋል። ከምሽት 3 እስከ ንጋት 12 ሰዓት የሚፀና ሰዓት እላፊም ታውጇል።

ሱቆች፣ ምግብ ቤቶችና መጠጥ ቤቶች ምሽት 2 ሰዓት ላይ በራቸውን እንዲዘጉ ታዝዘዋል።

የፖሊስ ሚኒስትሩ ቤኪ ሴሌ ምግብ ቤቶች ሕግ ጥሰው የሚገኙ ከሆነ የንግድ ፈቃዳቸውን ይነጠቃሉ ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

አልፎም የተላለፈውን ደንብ ጥሰው በሻይ ስኒ 'ካቲካላ' ሲሸጡ የተገኙ በሕግ ይቀጣሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

"በሻይ ስኒ አልኮል እንዳትሸጡ። 0% አልኮል የሚል ምልክት ባላቸው ኮዳዎችውም አልኮል ስትሸጡ እንዳትታዩ። ማታለያ መንገዶቻችሁን እናውቃለን። እንዳትሞክሯት" ብለዋል ሚኒስትሩ።

"በሻይ ብርጭቆ ውስጥ ከሻይ ውጭ ሌላ ነገር ብናገኝ - የንግድ ፈቃዳችሁን ነው የምንነጥቃችሁ።"

ደቡብ አፍሪካ ባለፈው ሚያዚያና ግንቦት ከኮቪድ-19 ጋር በተገናኘ ገደብ ጥላ ነበር።

በወቅቱ አልኮልና ትምባሆ በየትኛው ሥፍራ እንዳይሸጡ ተከልክሎ እንደነበር ይታወሳል።

ይህ ያልተዋጠላቸው ምግብ ቤቶች ለደንበኞቻቸው በሻይና ቡና ስኒ እንዲሁም በሌሎች ኮዳዎች ጠንከር ያለ ካቲካላ ሲቸበችቡ ቆይተዋል።

ባለፈው ሰኞ የተላለፈው አልኮል ያለመሸጥ ገደብ እስከሚቀጥለው ቀር አጋማሽ ድረስ ይቆያል።

የሃገሪቱ ፖሊስ ከወታደሮች ጋር በመተባበር ይህን እንዲያስፈፅም ታዟል።

ያሳለፍነው እሁድ ደቡብ አፍሪካ አንድ ሚሊዮን በኮቪድ የተያዙ ሰዎች ያሉባት ብቸኛዋ የአህጉሪቱ ሃገር ሆናለች።

ወረርሽኙ ወደ ሃገሪቱ ከገባበት ወርሃ መጋቢት ጀምሮ 27 ሺህ ሰዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ሞተዋል።

በሃገሪቱ ኮሮናቫይረስ እንደ አዲስ አገርሽቷል።

ባለፈው ሳምንት ብቻ 11 ሺህ 700 በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ተመዝግበዋል። ይህም እስከዛሬ ከታየው ቁጥር ከፍተኛው ነው ተብሏል።