አርጀንቲና ጽንስ ማቋረጥን ፈቀደች

ሕጉን የሚደግፉና የሚቃወሙ አርጀንቲናዊያን ከኮንግረስ መናኸሪያ ወጣ ብሎ ድምፃቸውን እያሰሙ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአርጀንቲና ሴናተሮች እስከ 14ኛው ሳምንት ድረስ ጽንስ ማቋረጥን መፈቀድ አለበት በሚለው ሕግ ዙሪያ ውይይትና ክርክር ካካሄዱ በኋላ መፍቀዳቸው ተሰምቷል።

38 ሴናተሮች ህጉን ደግፈው ድምጽ የሰጡ ሲሆን 29 ደግሞ መቃወማቸው ተሰምቷል።

አሁን ባለው ሁኔታ አርጀንቲና ውስጥ ጽንስ ማቋረጥን የሚፈቀደው እናት ከተደፈረችና የጤናዋ ሁኔታ አስጊ ከሆነ ብቻ ነው።

ሕጉ 'ቻምበር ኦፍ ዴፒዩቲስ' በተሰኘው የአርጀንቲና መንግሥት መዋቅር አልፎ ነበር ወደ ሴናተሮች ምክር ቤት የደረሰው።

በፈረንጆቹ 2018 የአርጀንቲና ሴናተሮች ሕጉን ለማፅደቅ ድምፅ ሰጥተው በጠባብ ውጤት ሳይፀድቅ ቀርቶ ነበር።

የመብት ተሟጋቾች ሕጉ እንዲፀድቅ ለዓመታት ሲወተውቱ የነበረ ሲሆን አሁን ሕጉ የፀደቀው የዛሬ ዓመት ሴናተሮቹ በጠባብ የድምጽ ብልጫ ውድቅ እንዲሆን ባደረጉ በዓመቱ ነው።

የአርጀንቲና ፕሬዝዳንት አልቤርቶ ፈርናንዴዝ ሕጉን ደግፈው ንግግር አድርገው ስለነበር ለበርካታ የመብት ተሟጋቾች ምናልባትም በስተመጨረሻ ጽንስ ማቋረጥ የሚፈቅደው መመሪያ እውን ሊሆን ይችላል የሚል ፍንጭ ሰጥቷቸው ነበር።

ሕጉ መጽደቁ በላቲን አሜሪካ ትልቅ ዜና ሆኗል። ሌሎች የላቲን አሜሪካ አገራትም አርጀንቲናን ፈለግ ይከተላሉ የሚል ተስፋ አጭሯል።

የላቲን አሜሪካ ቀጣና ሃገራት በአብዛኛው የካቶሊክ እምነት ተከታይ በመሆናቸው ጽንስ ማቋረጥ ክልክል ነው።

"ዛሬ ቀኑ የተስፋ ነው። ፍትሃዊ ያልሆኑ ሞቶችን የምናስወግድበት ቀን ነው ዛሬ" ብለዋል ኤኤፍፒ ዜና ወኪል ያነጋገራቸው ሴናተር ኖርማ ዱራንጎ።

በላቲን አሜሪካ ትልቅ ተሰሚነት ያላት የካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ጽንስ ማቋረጥን አትፈቅድም።

ቤተ-ክርስትያኗ ሴናተሮች ረቂቁን ውድቅ እንዲያደርጉትም ጥሪ አቅርባ ነበር።

አርጀንቲናዊው የሮማ ካቶሊክ ሊቀ-ጳጳስ ፍራንሲስ ክርክሩ ከመጀመሩ ሰዓታት በፊት በትዊተር ገፃቸው "እያንዳንዱ የተገፋ ሕፃን የፈጣሪ ልጅ ነው" ሲሉ ፅፈዋል።

ሕጉን የሚደግፉና የሚቃወሙ አርጀንቲናዊያን ከኮንግረስ መናኸሪያ ወጣ ብሎ ድምፃቸውን እያሰሙ ናቸው።

አሁን ባለው ሁኔታ አርጀንቲና ውስጥ ጽንስ ማቋረጥ የሚፈቀደው እናት ከተደፈረችና የጤናዋ ሁኔታ አስጊ ከሆነ ነው።

በሌላ በኩል በኤል-ሳልቫዶር፣ ኒካራግዋ እና በዶሚኒካን ሪፐብሊክ ጽንስ ማቋረጥ ሙሉ በሙሉ የተከለከለ ነው።

በተቀሩት የላቲን አሜሪካ ሃገራት ደግሞ ጽንስ ማቋረጥ የሚፈቀደው በጣም ልዩ በሆኑ ጉዳዮች ጊዜ ብቻ ነው።

ከሰፊው የደቡብ አሜሪካ ቀጣና ዩራጓይ፣ ጉያና እና አንዳንድ የሜክሲኮ ክልሎች ሴቶች ፅንስ ማስወረድ ከፈለጉ እንዲጠይቁ ያበረታታሉ።

ባለፈው ጊዜ ረቂቁ ለአርጀንቲና ኮንግረስ ቀርቦ 38 ለ31 በሆነ ድምፅ ነው የወደቀው።