ኮሮናቫይረስ፡ በቻይናዋ ዉሃን 500 ሺህ ሰዎች በኮቪድ-19 ተይዘው ነበር ተባለ

ከቻይናዋ ከተማ ዉሃን ነዋሪዎች መካከል 5 በመቶ ያሕሉ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከቻይናዋ ከተማ ዉሃን ነዋሪዎች መካከል 5 በመቶ ያህሉ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ነበር ሲል የቻይና በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል ተመራማሪዎች ጥናት ይፋ አደረገ።

በዚህ ጥናት መረጃ መሰረት የዉሃን ሕዝብ ብዛት 11 ሚሊዮን ሲሆን ከእነዚህም መካከል 500,000 ያህሉ በቫይረሱ ተይዘው ነበር ማለት ነው።

የዚህ ጥናት ውጤት እውነት ሆኖ ከተገኘ የዉሃን ግዛት ባለሥልጣናት በቫይረሱ ተይዘዋል በሚል ከገለፁት ቁጥር በ10 እጥፍ የሚበልጥ ሰው በኮሮና ተህዋሲ ተጠቅቶ ነበር ማለት ነው።

ዉሃን እስካሁን ድረስ በቫይረሱ መያዛቸውን የተናገረችው 50,354 ሰዎችን ብቻ ነው።

በቻይና ቫይረሱ ኖሮባቸው ነገር ግን ምንም ዓይነት ምልክት የማያሳዩ ሰዎች (Asymptomatic cases) አይቆጠሩም።

ይህ ጥናት ይፋ የተደረገው የዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ቡድን የኮቪድ-19 መነሻ የሆነችውን ዉሃንን ለመጎብኘትና ምርመራ ለማድረግ ከመምጣታቸው ቀደም ብሎ ነው።

የዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችና ገለልተኛ አካልን ለመቀበል ዳተኛ ከነበረው ከቻይና መንግሥት ጋር ለረዥም ጊዜ ከተደረገ ድርድር በኋላ በሚቀጥለው ወር ምርመራቸውን ለመጀመር ወደ ግዛቲቱ ይመጣሉ።

ቻይና በኮሮናቫይረስ የተያዙ ዜጎቼ በሚል ይፋ ያደረገችው ቁጥር ላይ ጥርጣሬ የገባቸው አካላት፣ አገሪቱ የኮሮናቫይረስ ቁጥሮች ላይ ግልጽነት ይጎድላታል በሚል ሲተቿት ነበር።

ለዚህ ጥናት በዉሃን ከ34,000 ሰዎች እንዲሁም ከሁቤ፣ ቤይዢንግ፣ ሻንጋይ እንዲሁም አራት ሌሎች አውራጃዎች ናሙናዎች መወሰዳቸውን የበሽታ መቆጣጠር እና መከላከል ማዕከሉ በዊቻት ላይ የለቀቀው መግለጫ ያስረዳል።

ተመራማሪዎቹ በዉሃን ብቻ ከተወሰዱ ናሙናዎች 4.43% አንቲቦዲ ያገኙ ሲሆን፣ በ ሁቤይ ድንበር ከተማ ደግሞ የስርጭት መጠኑ 0.44% መሆኑን ደርሰውበታል።

ጥናቱ አክሎም ከሁቤይ ውጪ ከተመረመሩ 12,000 ሰዎች መካከል ሁለቱ ብቻ አንቲቦዲ አዳብረው ተገኝተዋል ብሏል።

ጥናቱ የተካሄደው ቻይና የመጀመሪያውን ዙር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተቆጣጠረች ከወር በኋላ ነው።

ይህ ጥናት በማጠቃለያው ላይ እንዳስቀመጠው በኮሮና ተህዋሲ የተያዙ ቻይናውያን ቁጥር ከዉሃን ውጪ አነስተኛ ሲሆን ይህም ሊሆን የቻለው በግዛቲቱ የተደረገው ጠንካራ የመከላከል ሥራ ወረርሽኙ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በስፋት እንዳይሰራጭ ስላደረገው ነው ብሏል።

እየተጠናቀቀ ባለው በዚህ የፈረንጆች ዓመት መጀመሪያ ላይ በዉሃን የገበያ ስፍራ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ ይታወሳል።

ከዚያ ጊዜ ወዲህ በዚህ የገበያ ስፍራ የኮሮናቫይረስ ከእንስሳት ወደ ሰው ሳይተላለፍ አልቀረም የሚል መላምት ሲነገር ቆይቷል።

ነገር ግን አሁን ባለሙያዎች ቫይረሱ ከዚያ አካባቢ መነሻውን አድርጎ ሳይሆን፣ በበርካታ ሰዎች ላይ በስፋት የተሰራጭቶ ሊሆን ይችላል እያሉ ነው።