ቻይና ስለ ውሃን የኮሮናቫይረስ ስርጭት የዘገበችውን አሰረች

የፎቶው ባለመብት, YOUTUBE/SCREENSHOT
ዛንግ ዝሀን የተባለች ግለሰብ የውሃን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ከዘገበች በኋላ የአራት ዓመት እስር ተፈረደባት።
የ37 ዓመቷ የቀድሞ ጠበቃ የጋዜጠኛ ሚናን በመጫወት ስለ ውሃን ዘገባ ከሠራች በኋላ ግንቦት ላይ ነበር የታሰረችው።
የተከሰሰችው “ጸብ በማጫር እና ችግር በመፍጠር ነው”። ቻይና ብዙ የመብት ተሟጋቾችን የምታስረው በዚህ ክስ ነው። ከታሰረች በኋላ ለወራት የረሀብ አድማ በመምታቷ ጤናዋ አሳሳቢ ሀኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠበቃዋ ተናግረዋል።
ቻይና ብዙ በተለያየ ሙያ የተሰማሩ ነገር ግን ዘገባ የሚሠሩ (ሲቲዝን ጆርናሊስትስ) አስራለች።
ቻይና ውስጥ ነፃ መገናኛ ብዙኃን እንደሌሉና የመብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ እንደሚታሰሩም ይዘገባል። ከዛንግ ጠበቆች አንዱ ረን ኩዋኑ ለኤኤፍፒ እንዳሉት “እስር ሲፈረድባት በጣም አዝናለች”።
ፍርድ ቤት የነበሩት እናቷ ውሳኔውን ሲሰሙ እየጮሁ ያለቅሱ ነበር። ዛንግ ከመታሰሯ በፊት ለአንድ ገለልተኛ ፊልም ሠሪ እንደገለጸችው፤ ወደ ውሃን ለመሄድ የወሰነችው ነዋሪዎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የጻፉትን ካነበበች በኋላ ነው።
በወረርሽኙ ወቅት ውሃን ውስጥ በየጎዳናው እና ሆስፒታሉ ያየችውን ስትዘግብ ነበር። ባለሥልጣኖች ቢያስፈራሩዋትም መረጃውን ከማጋራት አልተቆጠበችም።
ጽሑፎቿን በርካቶች ይቀባበሉትም ነበር። ዘገባዋ ገለልተኛ ጋዜጠኞች መታሰራቸውን እና መንገላታታቸውንም እንደሚዳስስ የቻይና የሰብአዊ መብት ተሟጋች አስታውቋል።
“አመጸኛ ነኝ። እውነታውን እመዘግባለሁ። ለምን እውነታውን ማጋለጥ አልችልም? አላቆምም። አገሬ ወደኋላ እንድትመለስ አልፈልግም” ስትል የሚያሳይ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል ቢቢሲ አግኝቷል።
ፖሊስ በቁጥጥር ስር ካዋላት በኋላ በዊቻት፣ ትዊተር እና ዩቲዮብ ሐሰተኛ መረጃ አሰራጭታለች ሲል ከሷታል።
እስሯን በመቃወም የረሀብ አድማ ስትመታ በግድ እንድትመገብ መደረጓን ጠበቃዋ ተናግረዋል። ራስ ምታት፣ ድካምና ሆድ ቁርጠት እንዳለባትና ሥነ ልቦናዋም እንደተጎዳ አክለዋል።
ከዚህ ቀደም የሆንግ ኮንግ የመብት ተሟጋቾችን በመደገፏ ታስራ ነበር። በቻይና ሰብአዊ መብት ድርጅት የሚሠሩት ሊዮ ላን እንደሚሉት፤ የዛንግ መታሰር እጅግ አሳሳቢ ነው።
“የተፈረደባት እስር ረዥም ነው። የቻይና መንግሥት ጸጥ ሊያስብላትና ሌሎችን ዜጎችም ሊያስፈራራ ቆርጦ ተነስቷል” ብለዋል።
ወረርሽኙን በተመለከተ የዘገቡ ሰዎች መታሰራቸው በጣም እንደሚያስጨንቃቸውም አክለዋል። ስለ ውሃን የጻፉት ሊ ዢሀን፣ ቺን ኩውቺ እና ፋንግ ቢን የዓመቱ መባቻ ላይ ተሰውረዋል።
ሊ ያለበት ከታወቀ በኋላ በግድ ለይቶ ማቆያ እንዲገባ መደረጉን ተናግሯል። ቺን መንግሥት እየተቆጣጠረው ከቤተሰቡ ጋር እየኖረ ሲሆን ፋንግ ግን እስካሁን የት እንደደረሰ አልታወቀም።












