ኮሮናቫይረስ፡ ትራምፕ ለአሜሪካዊያን በነፍስ ወከፍ 600 ዶላር እንዲሰጥ ፈቀዱ

በርካታ አሜሪካውያን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሥራቸውን በማጣታቸው የመንግሥትን እጅ ጠባቂ ሆነዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በኮሮናቫይረስ ምክንያት አቅማቸው ለደከመ አሜሪካዊያን የሚሆን ድጎማና ሌሎችም ወጪዎች የተካተቱበት ማዕቀፍ ላይ ፊርማቸውን አሳርፈዋል።

ፕሬዝደንቱ አልፈረምም ማለታቸውን ተከትሎ የአሜሪካ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ይዘጋሉ ተብሎ ተሰግቶ ነበር።

ትራምፕ ለአሜሪካ ሕዝብ 600 ዶላር አይበቃውም 2 ሺህ እንጂ ብለው ላለመፈረም ቃል ገብተው ነበር።

በዚህ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሥራ አጥ አሜሪካዊያን ያለምንም ጥቅም ቀናት ለማሳለፍ ተገደው ነበር።

የአሜሪካ ኮንግረስ ለወራት ከመከረና ከዘከረ በኋላ ባለፈው ሳምንት 900 በሊዮን ዶላር የያዘ ድጎማ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።

ድጎማው ከ2.3 ትሪሊዮን ዶላር በጀት የተቀነጨበ ሲሆን 1.4 ትሪሊዮን ዶላር ደግሞ ለመንግሥት ወጭ ይሆናል ተብሏል።

ትራምፕ ሰኞ እኩለ ለሊት ፊርማቸውን ባያሳርፉ ኖሮ የአሜሪካ መንግሥት ይዘጋ ነበር።

14 ሚሊዮን ገደማ ሥራ የሌላቸው አሜሪካዊያን ፊርማው በመዘግየቱ ምክንያት ከመንግሥትሌምንም ዓይነት ደጎማ ሳያገኘዑ ከርመዋል።

አሁን ግን ከመንግሥት ጥቅማ ጥቅም ማግኘት ይጀምራሉ።

ለእያንዳንዱ አሜሪካዊ 2 ሺህ ዶላር ይሰጠው የሚል ማዕቀፍ ካለመጣችሁ 'አንገቴን ለካራ' ብለው የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ በምን ምክንያት ሐሳባቸውን እንደቀየሩ አልታወቀም።

ትራምፕ፤ ኮንግረስ ውስጥ ካሉ የሁሉቱም የአሜሪካ አውራ ፓርቲዎቻ አባላት ጫና ሲደርስባቸው ነበር።

ሪፐብሊካኑ ሴናተር ሚት ሮምኒ በስተመጨረሻም ማዕቀፉ ሕግ ሆኖ በመፅደቁ 'እፎይታ' እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

ተመራጩ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ተሰናባቹ ፕሬዝደንት ትራምፕ ፊርማቸውን የማያሳርፉ ከሆነ 'አደጋው የከፋ' ሊሆን እንደሚችል ሲያስጠነቅቁ ነበር።

ጠንከር ያሉ ቃላት ያዘለ መግለጫ የለቀቁት ባይደን ትራምፕ ፊርማን ለማሳረፍ አሻፈረኝ ማለታቸው 'ኃላፊነት የጎደለው' ሲሉ ዘልፈዋቸው ነበር።

የኮሮናቫይረስ ድጎማና ሌሎችም በርካታ በጀቶች የተካተቱበት የገንዘብ ማዕቀፍ ወደ አሜሪካ ኮንግረስ ቀርቦ በአብላጫ ድምፅ ቢፀድቅም ትራምፕ ይህ "ውርደት" ነው ሲሉ ገልፀውት ነበር።

አልፎም ማዕቀፉ "በአላስላፈጊ በጀቶች የተሞላ ነው" ሲሉ ትራምፕ አጣጥለውታል።

ማዕቀፉ በዓመት ከ75 ሺህ ዶላር በታች ለሚያገኙ አሜሪካዊያን 600 ዶላር ይሰጣቸው ይላል። ትራምፕ ደግሞ 2 ሺህ ነው የሚገባው ለአሜሪካ ሕዝብ ይላሉ። ነገር ግን ይህ ሐሳባቸው ከሳቸው ፓርቲ ሆነ ከዴሞክራቶች ተቀባይነት አላገኘም።

ትራምፕ ሐሳብ በርካታ ፖለቲከኞችን አስደንቋል፤ አስደንግጧል።

ተንታኞች ፕሬዝደንቱ በኮሮናቫይረስ ምክንያት አቅማቸው ለደከመ አሜሪካዊያን እንዲሆን ድጎማ ይሰጥ ተብሎ ክርክር ሲደረግ አንዳችም ሐሳብ አላነሱም፤ አሁን ደርሰው ይህን ማድረጋቸው ተገቢ አይደለም ሲሉ ይተቻሉ።

የዶናልድ ትራምፕ አጋር የሆኑት የገንዘብ ሚኒስትሩ ስቲቨን መኑቺን 600 ዶላሩን ደግፈው ከጥቂት ሳምንታት በፊት አስተያየት ሲሰጡ ነበር።