ኮሮናቫይረስ ፡ አዲሱ የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያ በተለያዩ አገራት ውስጥ እየተገኘ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በመጀመሪያ በዩናይትድ ኪንግደም የተገኘውና በመዛመት አቅሙ ከቀደመው የበለጠ ነው የተባለው አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ በበርካታ የአውሮፓ አገራት እንዲሁም በካናዳና በጃፓን መገኘቱ ተረጋገጠ።
በስፔን፣ በስዊትዘርላንድ፣ በስዊዲንና በፈረንሳይ የተገኘው ቫይረስ ከዩናይትድ ኪንግደም ከመጡ ሰዎች ጋር የተገናኘ መሆኑም ታውቋል።
በካናዳዋ ኦንታሪዮ ውስጥ አዲሱ አይነት የኮቪድ-19 ቫይረስ የተገኘባቸው ጥንዶች ደግሞ የታወቀ ከዚህ ቀደም ወደ ሌላ አገር የተደረገ የጉዞ ታሪክም ሆነ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ እንደሌላቸው ባለስልጣናት ተናግረዋል።
በግዛቷ ውስጥ ነዋሪ ከሆኑት የውጭ ዜጎች በስተቀር ጃፓን በአብዛኞቹ ወደ አገሯ በሚገቡ ተጓዦች ላይ ከሰኞ ጀምራ ለአንድ ወር የሚቆይ እግዳ ትጥላለች።
ጃፓን አምስት ከዩናይትድ ኪንግደም የመጡ ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱን ካረጋገጠች በኋላ ተጨማሪ ሁለት ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል ከእነሱም ውስጥ አንደኛው በአገር ውስጥ በበሽታው መያዙ ታውቋል።
አዲሱ የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያ መገኘቱ ከታወቀ በኋላ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አገራት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የጉዞ እገዳዎችን እየጣሉ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በርካታ የአውሮፓ ሕብረት አገራት ወረርሽኙን ለመከላከል የሚሰጠው ክትባት በአህጉሪቱ በተቀናጀ ሁኔታ ዛሬ እሁድ መሰጠት ከመጀመሩ በፊት ዜጎቻቸውን መክተብ ጀምረዋል።
ተመራማሪዎች እንደሚሉት አዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ በመጀመሪያ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የተገኘው አገሪቱ ባላት ጠንካራ የበሽታ ቅኝት ሥርዓት ምክንያት ነው።
ምንም እንኳን አዲሱ የቫይረስ ዝርያ ቀደም ካለው በበለጠ በስፋት የመዛመት አቅም አለው ቢባልም በተያዙት ሰዎች ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት አንጻር ግን አደገኛ ነው ማለት እንደማይቻል ባለሙያዎች ገልጸዋል።
አዲሱ የቫይረስ ስርጭት
ካናዳ ውስጥ ቫይረሱ የተገኘባቸው ጥንዶች በአሁኑ ጊዜ እራሳቸውን ለይተው ሚገኙ ሲሆን፤ በጃፓን የተገኙት ሁለት ህሙማን ደግሞ አንደኛው ከ10 ቀናት በፊት ከዩናይትድ ኪንግደም የተመለሰ የአውሮፕላን አብራሪና ሌላኛዋ ከቤተሰቦቿ መካከል አንዳቸውም ወደዚያ የተደረገ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው የ20 ዓመት ሴት ናት።
በስፔን ውስጥ በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ የተያዙ አራት ሰዎች እንዳሉ ተረጋግጧል። አራቱም ከዩናይትድ ኪንግደም የመጡ ሲሆን አንዳቸውም የከፋ ህመም አላጋጠማቸውም።
ስዊትዘርላንድ ደግሞ ሦስት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ያገኘች ሲሆን ሁለቱ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የብሪታኒያ ዜጎች ናቸው።
ስዊትዘርላንድ የበረዶ መንሸራተቻ የመዝናኛ ስፍራዎችን በዚህ የገናና የአዲስ ዓመት ጊዜ ክፍት በማድረግ በአውሮፓ ብቸኛዋ አገር ስትሆን፤ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሺህ የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ከብሪታኒያ ወደ ግዛቷ ገብተዋል።
የስዊዲን የጤና ባለስልጣናት አንድ ከዩናይትድ ኪንግደም የተመለሰ የአገሪቱ ዜጋ ላይ አዲሱ የቫይረስ ዝርያ የተገኘበት መሆኑን አስታውቀው እራሱን ለይቶ እንዲቆይ መደረጉ ተነግሯል።
ፈረንሳይም አዲሱን የቫይረስ ዝርያ ማግኘቷን አረጋግጣለች። የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር እንዳለው ቫይረሱ የተገኘበት ግለሰብ ከሳምንት በፊት ከለንደን የተመለሰ መሆኑ ታውቋል።
ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ነዋሪ የነበረው ግለሰብ ምንም አይነት ምልክት የማያሳይ ነገር ግን በሽታውን የሚያስተላልፍ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጾ፤ እራሱን ለይቶ እንዲቆይ ተደርጓል ብሏል።
ፈረንሳይ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ አዲሱ የቫይረስ ዝርያ መገኘቱ ከተረጋገጠ በኋላ ከአገሪቱ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር የዘጋች ሲሆን በአውሮፓ ሕብረት ዜጎች ላይ ጥላው የነበረውን የጉዞ ዕገዳ ግን በማንሳት የምርመራ ውጤት ለሚያቀርቡ ሰዎች በሯን ከፍታለች።
በተጨማሪም በዴንማርክ፣ በጀርምን፣ በጣሊያን፣ በኔዘርላንድስና በኦስትሪያ ውስጥም አዲሱ የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያ መገኘቱ ቀደም ሲል ተገልጿል።
አዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ
አዲሱ የቫይረስ ዝርያ በመስከረም ወር ላይ በደቡባዊ እንግሊዝ ውስጥ የተገኘ ሲሆን፤ ይህም በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በለንደን ከተማ፣ በደቡብ ምሥራቅ እንግሊዝና በምሥራቅ እንግሊዝ ውስጥ ለታየው በበሽታው ለተያዙ ሰዎች አሃዝ መጨመር ምክንያት ነው ተብሏል።
የአገሪቱ የስታትስቲክስ ጽህፈት ቤት እንደሚገምተው በተጠቀሱት አካባቢዎች በኮሮናቫይረስ ከተያዙት ሰዎች መካከል ሁለት ሦስተኛው አዲሱ ዝርያ ሳይገኝባቸው አይቀርም።
አገራት የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት መስጠት በጀመሩበት በዚህ ጊዜ አዲስ የቫይረሱ ዝርያ መገኘቱ አሳሳቢ ቢሆንም፤ ለወራት ክትባቶችን በማዘጋጀት ምርምር ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች ግን በቀዳሚነት የተቀመጡት ክትባቶች ቫይረሱን በመከላከል በኩል እንደሚጠቅሙ ዕምነት አላቸው።
















