ኮሮናቫይረስ፡ ፈረንሳይ በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ የተያዘ የመጀመሪያውን ግለሰብ ማግኘቷን አረጋገጠች

ፈረንሳይ በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ የተያዘ የመጀመሪያውን ግለሰብ ማግኘቷን አረጋገጠች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ፈረንሳይ በቅርቡ በዩናይትድ ኪንግደም ተገኘ የተባለውና ከነባሩ በጣም ተላላፊ በሆነው አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ የተያዘ የመጀመሪያውን ሰው ማግኘቷን አረጋገጠች።

የፈረንሳይ የጤና ሚኒስቴር እንዳለው ግለሰቡ የፈረንሳይ ዜጋ ሲሆን ከሰባት ቀናት በፊት ከለንደን ወደ አገሪቱ የገባ ነው። በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠውም ከአምስት ቀናት በፊት በሆስፒታል ምርመራ ከተደረገለት በኋላ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ሚኒስቴሩ እንዳለው ግለሰቡ የበሽታው ምልክት ያልታየበት ሲሆን አሁን ላይ በቤቱ ውስጥ ራሱን ለይቶ ይገኛል።

በቫይረሱ የተያዘው ግለሰብ ነዋሪነቱን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገ ፈረንሳዊ ሲሆን በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ አክሏል። ስለግለሰቡ የጤና ሁኔታ ግን በዝርዝር ያለው ነገር የለም።

በእንግሊዝ ተገኘ የተባለው አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ በርካታ አገራት ወደ አገሪቷ የሚያደርጉትን በረራ እንዲያግዱ አድርጓቸዋል።

ፈረንሳይም ድንበሯን ዘግታ የነበረ ሲሆን፤ መንገደኞች ከጉዟቸው በፊት እንዲመረመሩ በማድረግ ረቡዕ ዕለት የጣለችውን ገደብ አንስታለች።

በሺዎች የሚቆጠሩ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎችም የ'ኢንግሊሽ ቻናል'ን ለማለፍ እየተጠባበቁ የገናን በዓል በመኪናቸው ውስጥ ለማሳለፍ ተገደዋል።

ሌሎች አገራትም በአዲሱ ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን አግኝተዋል።

ጃፓን ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ አገሪቷ የገቡ አምስት መንገደኞች በቫይረሱ መያዛቸውን ያረጋገጠችው አርብ ዕለት ነበር።

ሆኖም ዴንማርክ፣ አውስትራሊያ እና ኔዘርላንድስ በበሽታው የተያዘ ሰው ማግኘታቸውን ያስታወቁት ቀደም ብለው ነው።

ባለፈው ሳምንት ፈረንሳይ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ጥላው የነበረውን የእንቅስቀሴ ገደብ አንስታለች፤ ይሁን እንጅ የቫይረሱ ስርጭት ባለመቀነሱ ሌሎች የተጣሉ ገደቦችን ለማንሳት አለመቻሉን መንግሥት አስታውቋል።

በዚህም ምክንያት እንደ መጠጥ ቤቶችና ምግብ ቤቶች ሁሉ ትያትርና ፊልም ማሳያ ቤቶችም ተዘግተው እንደሚቆዩ ተገልጿል።

በአገሪቷ የተጣለው የሰዓት እላፊም ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ጠዋት 12 ሰዓት ሆኖ ይቆያል።

ይህ የሰዓት እላፊ በገና በዓል ዋዜማ ላይ ተነስቶ የነበረ ቢሆንም በአዲስ ዓመት ዋዜማ ግን አይቀየርም ተብሏል።

ፈረንሳይ ወረርሽኙ ከተከሰተ አንስቶ ከ2.5 ሚሊየን ሰዎች በላይ በኮቪድ-19 መያዛቸውን ያረጋገጠች ሲሆን፤ 62 ሺህ ሞትም ተመዝግቦባታል።