ኮሮናቫይረስ ፡ አሜሪካ የዩናይትድ ኪንግደም መንገደኞች ኮቪድ እንዲመረመሩ የሚያስገድድ ደንብ አወጣች

ውሳኔው የተላለፈው በዩኬ በተገኘው አዲስ የኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አሜሪካ ከዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የሚመጡ የሁሉም አየር መንገድ ተሳፋሪዎች በ72 ሰዓታት ውስጥ ከኮቪድ- 19 ነፃ መሆናቸውን ማሳየት አለባቸው አለች።

ይህ ውሳኔ የተላለፈው በዩኬ በተገኘው አዲስ የኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ነው።

በመሆኑም ከመጭዎቹ ሁለት ቀናት በኋላ መንገደኞች የላብራቶሪ ምርመራ ውጤታቸውን የሚያሳይ የጽሁፍ ማስረጃ ለአየር መንገዶች ማሳየት አለባቸው ተብሏል።

የአሜሪካ የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) መንገደኞች ምርመራ እንዲያደርጉ የወሰነው ለአዲሱ የቫይረስ ዝርያ ምላሽ ለመስጠት የኒው ዮርክ ከተማ ለዓለም አቀፍ ተጓዦች የለይቶ ማቆያ ሕግ ማስተዋወቋን ተከትሎ ነው።

ሲዲሲ እንዳለው መንገደኞች በ'ፒሲአር' ወይም እንግዳ አካል ወደ ሰውነታችን ስለመግባቱ የሚጠቁሙ ሞለኪዩሎች [አንቲጂን] ምርመራ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን ማረጋጋጥ አለባቸው።

በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ምክንያት ሌሎች አገራትም ድንበሮቻቸውን ከዩኬ ለሚነሳ በረራ ዝግ አድርገዋል።

ይሁን እንጂ ዩኬም በቫይረሱ ፈጣን ስርጭት ሳቢያ የበርካታ እንግሊዛዊያን የውጭ አገር ጉዞ ክልከላን ጨምሮ ሌሎች ጥብቅ ገደቦችን ለመጣል ተገዳለች።

አሜሪካ ወረርሽኙ በተከሰተ መጀመሪያ አካባቢ አብዛኞቹ የውጭ አገር ዜጎች ወደ አገሯ እንዳይገቡ ካገደች በኋላ፤ የአሜሪካ አየር መንገዶች ወደ ዩኬ እና አውሮፓ የሚያደርጉት በረራ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰዋል።

አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ በጣም ገዳይ ስለመሆኑ ወይም ቫይረሱ ለክትባቱ የተለየ ምላሽ እንደሚሰጥ የሚያሳይ መረጃ እንደሌለ የጤና ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ነገር ግን ከነባሩ ቫይረስ በ70 በመቶ የመሰራጨት ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ተነግሯል።

ዩናይትድ እና ዴልታ አየር መንገድም በዩኬ በረራዎች ላይ ያሉ ሁሉም ተሳፋሪዎች ምርመራ እንዲያደርጉ እንደሚጠይቁ ያስታወቁት ሐሙስ ዕለት ነበር።