በሕንድ በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ የተያዙ ስድስት ግለሰቦች ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ የተያዙ ስድስት ግለሰቦች በሕንድ መገኘቱ ተገለፀ።
ስድስቱ ሰዎች ከዩናይትድ ኪንግደም በቅርብ የተመለሱ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን፣ ቫይረሱ ከተገኘባቸው በኋላ ራሳቸውን አግልለው እንዲቀመጡ መደረጉ ተነግሯል።
ሕንድ ከዩናይትድ ኪንግደም የሚመጣ ምንም አይነት የአየር ትራንስፖርትን ያገደችው ባለፈው ሳምንት ነበር።
ባለሙያዎች አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ በፍጥነት የሚዛመት መሆኑን ገልፀው ነገር ግን አደገኛነቱ እምብዛም ነው ብለዋል።
ሕንድ በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ያረጋገጠቻቸው ዜጎቿ ቁጥር 10 ሚሊዮን ያለፈ ሲሆን ይህም በተህዋሲው ከተጠቁ የዓለም አገራት መካከል ከአሜሪካ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል።
የሕንድ ባለሥልጣናት ከስድስቱ ግለሰቦች ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች መለየት መጀመራቸውን ገልፀዋል።
በሕንድ ከዩናይትድ ኪንግደም የመጡ መንገደኞች በአጠቃላይ በሁሉም የአየር መንገዶች አርቲ-ፒሲአር የተሰኘ የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንዲያደርጉ እንደሚደረግ በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።
ባለፈው ወር ብቻ 33,000 ያህል ግለሰቦች ከዩናይትድ ኪንግደም መምጣታቸው የተገለፀ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 114 በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል።
አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ በርካታ አገራት ከዩናይትድ ኪንግደም የሚመጡ ተጓዦች ላይ ገደብ እንዲጥሉ አስገድዷቸው ነበር።
ካናዳ፣ ጃፓን፣ ስፔን፣ ስዊዲን እና ፈረንሳይ አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ከተገኘባቸው አገራት መካከል ናቸው።
በዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣናት አገሪቱ "በጣም ከፍተኛ" የሆነ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው እንደሚኖር አስጠንቅቀዋል።
ሰኞ እለት ብቻ 41,385 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው በምርመራ ሲረጋገጥ ከእነዚህ መካከል 357 ያህሉ ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተዘግቧል።
አዲሱ ኮሮናቫይረስ ዝርያ መጀመሪያ የተገኘው በዩናይትድ ኪንግደም ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ከሃያ በሚበልጡ አገራት ውስጥ ተስፋፍቶ ይገኛል።












