ኮሮናቫይረስ ፡ የቻይና መንግሥት ያፈናቸው ድምጾች

ቻይና

የፎቶው ባለመብት, CHINA NEWS SERVICE

ቻይና ውስጥ የኮሮናቫይረስ ከተገኘ ዓመት ሊደፍን ነው። ቻይናን ከቫይረሱ ባሻገር ያሳሰባት በድረ ገጽ ላይ ስለ ወረርሽኙ የሚሰራጩ መረጃዎች ናቸው።

አሁን ላይ መንግሥት የሚቆጣጠረው መገናኝ ብዙሃን ወረርሽኙንም መረጃውንም የተቆጣጠረ ይመስላል።

ቻይና አሉታዊ ነው የምትለውን መረጃ በማፈን ትታወቃለች። መንግሥት ሳንሱር ሲያደርግ ይህ የወረርሽኝ ወቅት የመጀመሪያው አይደለም።

ሕዝቡ ግን የፕሮፓጋንዳን ግድግዳ አፍርሶ እውነታውን አደባባይ ለማውጣት ታግሏል።

ትችትን ሳንሱር ማድረግ

ዓመቱ መባቻ አካባቢ የቻይና ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሕዝቡ መንግሥት ሳርስን የሚመስል ቫይረስን ለመሸፋፈን እየሞከረ እንደሆነ እሮሮ ያሰማ ነበር።

መንግሥት ለወትሮው እንደ ዌቦ ባሉ የቻይና ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ትችቶችን ሳንሱር ያደርግ ነበር።

ኮሮናቫይረስን በተመለከተ ይሰራጩ የነበሩ ቅሬታዎች እጅግ ብዙ ስለነበሩ ግን መንግሥት ሊደብቃቸው አልቻለም።

በርካታ የሚዲያ ተቋሞች የምርመራ ዘገባ አትመዋል። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይም ዜናዎቹ ተሰራጭተዋል።

ቤይጂንግ ለዚህ ምላሽ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ጀመረችና ዘገባዎቹ ታፈኑ።

አምና ጥር ላይ ፕሬዘዳንት ዢ ዢፒንግ ከሕዝብና መገናኛ ብዙሃን ርቀው ነበር። በጋዜጦች የፊት ገጽ የፕሬዝዳንቱ ምስል ማተምም ቆመ።

ይህም ፕሬዝዳንቱ ከወቀሳ እየሸሹ ነው የሚል ትችት ቀሰቀሰ።

ብዙም ሳይቆይ ግን የቻይና ከፍተኛ ባለሥልጣናት የየክልሉ አመራሮች ስለ ኮሮናቫይረስ ትክክለኛ መረጃ ካልሰጡ "ታሪካዊ ውርደት" ይጠብቃቸዋል አሉ።

ከዚያም ወቀሳው ቫይረሱ የተነሳባት ዉሃን ከተማ ላይ ማነጣጠር ጀመረ። ዉሃን ስለወረርሽኙ ቀደም ብላ ማሳወቅ ነበረባት እየተባለ ተብጠለጠለች።

በየካቲት ዢ ዢፒንግ ዳግመኛ ወደ ሕዝብ እይታ ሲመለሱ ቻይና ከወረርሽኙ በማገገም ላይ ነበረች።

መረጃ አጋላጩ ዶክተር

ሊ ዌንበርግ በመላው ዓለም እውቅና ያገኘ የቻይና ዶክተር ነው። ሐኪሙ ስለ ኮሮናቫይረስ መረጃ በማጋለጥና ለባልደረቦቹ ሳርስን የሚመስል ቫይረስ እንደተነሳ በመናገር ነው የታወቀው።

ዶክተሩ የካቲት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ከመሞቱ በፊት "በሐሰተኛ ዜና ማኅበራዊ መዋቅርን በመረበሽ" ምርመራ ሲደረግበት እንደነበረ ተደርሶበታል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዌቦ ተጠቃሚዎች ዶክተሩን እንደሚደግፉ ቢናገሩም፤ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የለጠፉት መልዕክት ተሰርዟል።

ይህ የመረጃ ድምሰሳ ሕዝቡን አስቆጥቷል። ኢሞጂና ጥንታዊ የቻይና ስውር መልዕክት መለዋወጫን በመጠቀም ለዶክተሩ ያላቸውን ድጋፍ በመግለጽም ገፍተውበታል።

የታሰሩት ጋዜጠኞች

የቻይና ባለሥልጣኖች የኋላ ኋላ ዶ/ር ሊ "ሰማዕት" ነው ብለው እውቅና ሰጥተዋል። ሆኖም ግን ብዙ የመብት ተሟጋቾች ከቻይና ታሪክ ተሰርዘዋል።

ዉሃን ውስጥ ወረርሽኙ ሲቀሰቀስ ብዙ ዜጎች ዘገባ ሠርተው ለዓለም ሕዝብ መረጃ አድርሰዋል። ከእነዚህ መካከል ቺን ኪውሺ፣ ፋንግ ቢን እና ዛንግ ዛን በዋነኛነት ይጠቀሳሉ።

ዩቲዩብ ላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሰው የተመለከተው ቪድዮ ለቀዋል። ዉሃን ውስጥ ምን እንደተከሰተ የሚያሳዩ ምስሎችም አሰራጭተዋል።

ቻይና እነዚህን የዜጋ ጋዜጠኞች አስራለች። የተሰወሩም አሉ።

ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ እንዳለው፤ ከቤጂንግ ከሚወጣው መረጃ ውጪ ዜና ያሰራጩ ብዙ ጋዜጠኞች ታስረዋል።

ዩቲዩብ ቻይና ውስጥ ስለታገደ እነዚህ ጋዜጠኞች የሚያሰራጩት መረጃ ምን ያህል ሰው ጋር እንደደረሰ አያውቁም።

መረጃ ከሚያስተላልፉት አንዱ ሊ ዢሃን፤ የካቲት ላይ ቪድዮ ከለቀቀ በኋላ ለሁለት ወር አድራሻው ጠፍቶ ነበር።

ፖሊሶች በመኪና እያሳደዱት እንደሆነ ከገለጸ በኋላ ለሁለት ወራት ጠፍቶ ለይቶ ማቆያ እንደገባ የሚገልጽ ቪዲዮ ለቋል።

ከዚያ በኋላ ድምጹ አልተሰማም። ለይቶ ማቆያ እንደገባ የሚገልጸውን ቪድዮ እንዲቀርጽ መንግሥት ጫና እንዳሳደረበትም ይገመታል።

ድምጻቸው የታፈነ ወጣቶች

ከመጋቢት ወዲህ ቻይና ቫይረሱን እያሸነፈች እንደሆነ ለማሳየት እየሞከረች ቢሆንም ሳንሱር የተደረጉ መረጃዎች መኖራቸው ጥያቄ አጭሯል።

በተለይም ወጣት ቻይናውያን አፈናው ያስቆጣቸዋል።

ነሐሴ ላይ ተማሪዎች ቢመለሱም ከዩኒቨርስቲዎች አቅም በላይ በመሆኑ ተቃውሞ ተነስቷል።

ተቃውሞዎቹ በይፋ እንዳይሰሙ ቢደረግም የቻይና ወጣቶች ከተለመዱ ማኅበራዊ ገጾች ውጪ ሌሎች ገጾች በመፍጠር ቅሬታቸውን አስተጋብተዋል።

ድምጻቸውን ካሰሙባቸው ድረ ገጾች መካከል ሙዚቃ ማሰራጫዎች ይገኙበታል።

ቻይና የተጋነነ ተስፈኛ ምስል ለመፍጠር ሞክራለች። ሆኖም ግን ትክክለኛው መረጃ አልተገለጠም ብለው የሚያምኑ ብዙ ናቸው።

ቻይናዊቷ ጸሐፊ ፋንግ ፋንግ ዉሃን ስላለው ሕይወቷ በጻፈችው ተመስግናለች። በተቃራኒው የቻይና ብሔርተኞች "ክፉ ትርክት ወዳጅ" ሲሉ አብጠልጥለዋታል።

የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን አጉልተው የሚያሰሙት ድምጽ ስለ ቻይና በጎ ገጽታ የሚተርከውን ነው።

እውነተኛ ታሪክ ላይ ተመርኩዞ እንደተሠራ የተነገረለት የመጀመሪያው የቴሌቭዥን ድራማ የሴቶችን ሚና ያንኳሰሰ በመሆኑ ተተችቷል።

ቻይና የምትመርጠው ትርክት

ቻይና ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዞ ስሟ እንዳይነሳ ለማድረግ እየተጣረች ነው።

ወረርሽኙን ማሸነፍ ከቻለች ፖለቲካዊ መዋቅሯ ከምዕራባውያኑ የተሻለ ስለመሆኑ ማስረጃ እንደሚሆን ታምናለች።

'የዉሃን ኮሮናቫይረስ' በሚል የተጠራው ወረርሽኝ በዚህ ስያሜ እንዳይጠራ እንቅስቃሴ አድርጋለች።

የቻይና መገናኛ ብዙሃን የአሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም መንግሥታት ቫይረሱን መቆጣጠር እንዳልቻሉ የሚጠቁሙ ዘገባዎች አስተላልፈዋል።

እንዲያውም ኮቪድ-19ን 'የአሜሪካ ቫይረስ' ወይም 'የትራምፕ ቫይረስ' ብለው የሚጠሩም አልታጡም።

በሌላ በኩል የአሜሪካ ፖለቲከኞች ከጤና ሥርዓቱ ይልቅ ለምርጫ ቅስቀሳ ቅድሚያ እንደሰጡ በመግለጽ የዘገቡ የቻይና ሚዲያዎች አሉ።

ቻይና ወደ መጪው የፈረንጆች 2021 ስትሻገር ማስተጋባት የምትፈልገው ትርክት፤ 2020 በአንድነትና በብልጽግና መጠናቀቁን ነው።

በተቃራኒው ሌሎች አገሮች የበለጠ አለመረጋጋት እና ክፍፍል ይመጣል ብለው ይጠብቃሉ።