በክሮሺያ በደረሰ ርዕደ መሬት ሰባት ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ

ፐትሪንጃ 20 ሺህ ያህል ነዋሪዎች ያሏት ከተማ ስትሆን ከርዕደ መሬቱ አደጋ በኋላ የክሮሺያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመኖር ምቹ አይደለችም ሲሉ ተናግረዋል

የፎቶው ባለመብት, EPA

በክሮሺያ በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ በርካቶች ጉዳት ሲደርስባቸው ሰባት ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተገለፀ።

በማዕከላዊ ክሮሺያ የደረሰው ይህ ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል 6.4 ተመዝግቧል።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ርዕደ መሬቱ ከደረሰ በኋላ በጎበኟት ፐትሪንጃ ከተማ አንዲት የ12 ዓመት ታዳጊ መሟቷን አስታውቀዋል።

አምስት ሌሎች ሰዎች ደግሞ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ግሊና ከተማ መሞታቸውን ምክትላቸው ተናግረዋል።

ሰባተኛው ሟች የተገኙት ዛዚና ከተማ በርዕደመሬቱ ምክንያት በፈራረሰ ቤተ ክርስትያን ፍርስራሽ ስር መሆኑን የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የፐትሪንጃ ከንቲባ እንዳሉት የከተማዋ ግማሽ ክፍል ሙሉ በሙሉ ወደ ፍርስራሽነት የተቀየረ ሲሆን ሰዎች ከፍርስራሽ ውስጥ እየተፈለጉ እና እየተጎተቱ እየወጡ ነው።

ርዕደ መሬቱ እስከ ክሮሺያ ዋና ከተማ ዛግሬብ ድረስ የተሰማ ሲሆን ጎረቤት አገራት ሰርቢያ እና ቦሲኒያ እንዲሁም በርቀት የምትገኘው ጣልያን ድረስ መሰማቱም ተዘግቧል።

የክሮሺያ መገናኛ ብዙሃን በፐትሪንጃ ከተማ አንዲት ሴት ከፍርስራሽ ውስጥ ተጎትታ መውጣቷን ዘግበዋል።

"ሰዎችን ከመኪናቸው ውስጥ ጎትተን ስናወጣ ነበር፤ እንሙት እንጎዳ አናውቅም ነበር" ሲሉ ለአካባቢው የዜና ወኪል የተናገሩት የከተማዋ ከንቲባ ዳርኒኮ ዱምቦቪች ናቸው።

ፐትሪንጃ 20,000 ነዋሪዎች ያሏት ሲሆን ከንቲባዋ በድጋሚ አነስተኛ መጠን ያለው ርዕደ መሬት ከተሰማ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን "ሁሉም ሰው ተረብሿል፤ ዘመድ ወዳጁን ለመፈለግ ከወዲያ ወዲህ ይሯሯጣል" ሲሉ አክለዋል።

በቅርብ ርቀት በምትገኘው ሲሳክ ከተማም እንዲሁ ሰዎች በርዕደ መሬቱ የተነሳ ተጎድተው ወደ ሆስፒታል ማምራታቸው ተሰምቷል።

የአካባቢው ሆስፒታሎች በርካታ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለማከም ሲታገሉ ማስተዋሉን የብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣብያ ዘግቧል።

ከርዕደ መሬቱ አደጋ በኋላ የክሮሺያ ጠቅላይ ሚኒስትር 20 ሺህ ያህል ነዋሪዎች ያሏትን ፐትሪንጃ ከተማን የጎበኙ ሲሆን "ለመኖር ምቹ አይደለችም" ሲሉ ተናግረዋል።

መንግሥት ከተማዋን ዳግም ለመገንባት ቃል የገባ ሲሆን ነዋሪዎቿ ጊዜያዊ መጠለያ ይፈለግላቸዋል ሲል ተናግሯል።