አዲስ የተመረጡት አሜሪካዊ ሕግ አውጪ በኮቪድ-19 ሞቱ

ሉክ ሌቶው

የፎቶው ባለመብት, YOUTUBE

አዲስ የተመረጡት የሪፐብሊካን ሕግ አውጪ ሉክ ሌቶው በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ሕይወታቸው አለፈ። የ41 ዓመቱ ሉክ፤ በቫይረሱ ሳቢያ የሞቱ የመጀመሪያው የኮንግረስ አባል ናቸው።

የፊታችን እሑድ በይፋ ቃለ መሀላ ይፈጽማሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር። የተመረጡት የሉዊዝያና ወኪል ሆነው ነበር። በበሽታው መያዛቸውን ታህሳስ 18 አስታውቀው ሆስፒታል ገብተውም ነበር።

የሉዊዝያና አገረ ገዢ ጆን ቤል ኤድዋርድስ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ እለት ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ አዘዋል።

“እኔና ባለቤቴ በሉክ ሞት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልጻለን። ለቤተሰቡ መጽናናትንም እንመኛለን” ብለዋል አገረ ገዢው።

ገዢው የግዛቲቱ ተወካይ ሆነው አገራቸውን ሳያገለግሉ ሕይወታቸው በማለፉ የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል። ሉክ የሁለት ልጆች አባት ነበሩ።

ታህሳስ 19 ሆስፒታል ገብተው ከአራት ቀን በኋላ የጤና ሁኔታቸው አስጊ ስለሆነ የጽኑ ህሙማን ማቆያ ገብተዋል። በማቆያው ሳሉ ትላንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

“ቤተሰባችን በፀሎት እና በተለያየ መንገድ የደገፉንን ሰዎች ያመሰግናል። በዚህ ከባድ ወቅት ግላዊነታችን እንዲጠበቅም እንጠይቃለን” ሲል ቤተሰባቸው መግለጫ አውጥቷል።