አፍሪካ በ2020 የትኞቹን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን አጣች?

በዚህ ዓመት በሞት የተለዩ የተለያዩ ዝነኛ አፍሪካውያን ሰዎች ምስል

የፎቶው ባለመብት, Various

የፈረንጆቹ 2020ን መለስ ብሎ የሚያስታውስ ማንም ሰው ቢኖር ቀድሞ ወደ አእምሮው የሚመጣው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ነው። ከዚያ ውጪ ግን አፍሪካ በሞት ያጣቻቸው የተለያዩ ዝነኛ ሰዎች አሉ።

በእርግጥ አንዳንዶቹ አፍሪካ ፈርጦች የሞቱት ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ህመም መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል። ከእነዚህም መካከል ከእግር ኳስ ተጫዋች፣ ከሳይንስ ዘርፍ፣ ከሙዚቃው፣ ንግዱ፣ ከሕከምናው እና ከፖለቲካው መስኮች አፍሪካ የያጣቻቸውን አስር ሰዎችን ቢቢሲ መራርጧል።

Short presentational grey line

ሃጫሉ ሁንዴሳ፣ 34

በፖለቲካዊ ግጥሞቹ ከፍተኛ ዝናን ያተረፈው ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ በጥይት ተመትቶ ህይወቱ ያለፈው በዚሁ የፈረንጆች ዓመት ነበር። የእርሱን ሞት ተከትሎም በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞዎች ተቀስቅሰው ነበር።

ሃጫሉ ሁንዴሳ ተወልዶ ያደገው ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ አንድ መቶ ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምተገኘው አምቦ ከተማ ውስጥ ነው።

እናቱ ወይዘሮ ጉደቱ ሆራ፣ ሃጫሉ ከልጅነቱ ታሪክን መስማትና የመንገር ዝንባሌውንና ችሎታውን ጠንቅቀው ተረድተውት ስለነበር ከመጀመሪያው አንስቶ ያበረታቱት እንደነበር በተደጋጋሚ ሃጫሉ ያስታውሳል።

አባቱ አቶ ሁንዴሳ ቦንሳ ደግሞ ልጃቸው ሃጫሉ በትምህርቱ ዓለም ገፍቶ ዶክተር ወይም የዩኒቨርሲቲ መምህር እንዲሆንላቸው ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው።

ሃጫሉ ግን ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በፍቅሯ ለወደቀላት ሙዚቃ ነበር መላው ትኩረቱ። በአስራዎቹ እድሜው ላይ እያለ እንኳን የበርካቶችን ስሜት የሚኮረኩሩ ሙዚቃዎችን ይጫወት ነበር።

ሃጫሉ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ በ1995 ዓ.ም የ17 ዓመት ታዳጊ እንዳለ ታስሮ አምስት ዓመታትን አምቦ በሚገኘው እስር ቤት አሳልፏል።

ሃጫሉ ሁንዴሳ

እግር ኳስ: ፓፓ ቦውባ ዲዮፕ፣ 42

ሴኔጋላዊው እግር ኳስ ተጫዋች ለረዥም ጊዜ በሕመም ሲሰቃይ ከቆየ በኋላ የሞተው በኅዳር ወር ነበር። ፓፓ ለፉልሃም፣ ለዌስትሃም ዩናይትድ፣ ለበርሚንግሃም ሲቲ እና ለፈረንሳዩ ቡድን ሌንስ ተጫውቷል።

ይህ እግር ኳስ ተጫዋች ከፍተኛ እውቅና ያገኘው እኤአ በ2002 በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ላይ አገሩ ሴኔጋል ከፈረንሳይ ጋር በነበራት ግጥሚያ አሸናፊ የሆነችበትን ግብ በማስቆጠሩ ነበር።

በነበረበት ቡድን ውስጥም ትልቅ ስኬት ተብሎ የሚጠቀስለትም በ2008 ከፖርትስማውዝ ጋር ያደረገው የኤፍ ኤ ዋንጫ ግጥሚያ ነው።

ፓፓ ቦውባ ዲዮፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሳይንስ: ጊታ ራምጂ፣ 63

በዓለም ላይ ከፍተኛ እውቅናን ያገኘችው እና ኡጋንዳ የተወለደችው ደቡብ አፍሪካዊት ሳይንቲስት በመጋቢት ወር በኮቪድ-19 ምክንያት ነበር ህይወቷ ያለፈው።

ይህች ሳይንቲስት የምትታወቀው በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ለኤችአይቪ ያላቸው ተጋላጭነት ላይ በምትሰራው ጥናት ነው። ከሁለት ዓመት በፊትም በአውሮፓ ከሚገኝ ስመ ጥር ተቋም ምርጥ ሴት ሳይንቲስት ተብላ ተሸልማለች።

ጊታ ራምጄ

የፎቶው ባለመብት, Aurum Institute

ሙዚቃ: ማኑ ዲባንጎ፣ 86

ካሜሮናዊ ሳክስፎኒስት በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞተው በመጋቢት ወር ነበር። እኤአ በ1972 ጃዝ እና ፈንክ የሙዚቃ ስልቶችን ከባህላዊ ድምጾች ጋር ቀይጦ በሰራው ሙዚቃ እጅጉን ተወዳጅነትን አትርፏል።

ይህ የሙዚቃ ሰው ከሥራዎቹ መካከል አንዱን ማይክል ጃክሰን ሳያስፈቅደው እና ተገቢውን ክፍያ ሳይፈጽም በመጠቀሙ ክስ መስርቶበት ጉዳዩ ከፍርድ ቤት ውጪ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ማኑ ዲባንጎ በ2018 የሙዚቃ ሥራውን ሲያቀርብ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ንግድ: ሪቻርድ ማፖንያ 99

ሥራ ፈጣሪው አዛውንት የሞቱት ታኅሣስ ወር ላይ ነበር። በደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ዘመን የተጣለውን ገደብ በመጣስ የንግድ ኢምፓየር በመገንባታቸው "የችርቻሮ ንግድ አባት" በመባል ይታወቃሉ።

በደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች በብዛት በሚኖሩባት ሶዌቶ ከተማ፣ የመጀመሪያውን የቢኤምደብሊው መኪና መሸጫ እና ማፖንያ የገበያ አዳራሽን ገንብተዋል።

ሪቻርድ ማፖንያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሕክምና : ሃዋ አብዲ፣ 73

ሶማሊያዊቷ የህክምና ባለሙያ እና የመብት ተሟጋች የሞተችው በነሐሴ ወር ላይ ነበር። ይህች ሴት "የሶማሊያ ማዘር ቴሬሳ" በመባል ትታወቅ ነበር።

በ2011 በእስላማዊ ታጣቂዎች ሆስፒታሏ ጥቃት ሲደርስበት በአደባባይ ወጥታ በመቃወም በርካቶች አብረዋት እንዲሰለፉ ማድረግ የቻለች ናት። በዚህም የተነሳ ታጣቂዎቹ አካባቢውን ለቅቀው ለመውጣት ተገደዋል።

ሃዋ አብዲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፖለቲካ: ዳንኤል አራፕ ሞይ፣ 95

ከኬንያ ነጻነት በኋላ ሁለተኛው ፕሬዝዳንት ሆነው ከሃያ ዓመታት በላይ በብቸኝነት አገሪቱን የመሩት ዳንኤል አራፕ ሞይ በ95 ዓመታችው ነበር ያረፉት።

ፕሬዝዳንት አራፕ ሞይ የምሥራቅ አፍሪካዋን አገር ኬንያን በበላይነት ለ24 ዓመታት የመሩ ሲሆን፤ አገሪቱ ከእንግሊዝ ነጻነቷን ካገኘች በኋላ ስልጣን የያዙ ሁለተኛው ፕሬዝዳንት ነበሩ።

በሥልጣን ላይ በነበሩበትም ወቅት አገሪቱን በጠንካራ ክንዳቸው ገዝተዋል የሚባሉት ዳንኤል አራፕሞይ፤ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚተቿቸው አሉ።

ዳንኤል አራፕ ሞይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ረ አፓርታይድ ንቅናቄ መሪ፣ ዚንድዚ ማንዴላ፣ 59

የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሪዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ትንሽ ልጅ በኮቪድ-19 ምክንያት የሞቱት በሐምሌ ወር ነበር።

የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚደንት ኔልሰን ማንዴላ እና የፀረ አፓርታይድ ተሟጋቿ ዊኒ ማዲኪዜላ ማንዴላ ሴት ልጅ የሆኑት ዚንዲዚ ማንዴላ ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስም በዴንማርክ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።

ዚንዲዚ በዴንማርክ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ከአምስት ዓመታት በፊት ሲሆን በላይቤሪያ ሞንሮቪያ ደግሞ ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል።

ዚንዲዚ ማንዴላ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ኪነ ጥበብ: ኒኪታ ፐርል ዋሊግዋ፣ 15

ከኡጋንዳ ዝቅተኛ ከሚባለው መንደር ወጥታ ዓለምን ስላስደመመቸው ታዳጊ የቼዝ ተጫዋች ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው ኩዊን ኦፍ ካትዌ ላይ ተዋናይት የነበረችው የ15 ዓመቷ ታዳጊ ህይወቷ የያለፈው በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት ነበር።

ኒኪታ ፐርል ዋሊግዋ በጭንቅላት ዕጢ ስትሰቃይ ነበር ተብሏል።

ከአራት ዓመታት በፊት ለዕይታ የበቃው ይህ ፊልም ፊዮና ሙቴሲ የተባለች ታዳጊ የነበራትን የቼዝ ችሎታ የሚያስቃኝ ነው።

ታዋቂዋ ኬንያዊት ተዋናይት ሉፒታ ኒዮንግ የታዳጊዋ እናት ገፀ ባሕርይ ተላብሳ የምትጫወት ሲሆን ሌላኛው ታዋቂ ተዋናይ ዴቪድ ኦየልዎ ደግሞ የቼዝ መምህሯ ሆኖ ተውኗል።

ኒኪታ የፊዮናን ጓደኛ ግሎሪያን ገፀባህርይ ወክላ የተወነች ሲሆን፤ የቼዝንም ሕጎች ለመጀመሪያ ጊዜ ያስረዳቻት እሷ ነበረች።

ኒኪታ ፐርል ዋሊግዋ

የመብት ተሟጋች: ሊና ቤን ምሄኒ፣ 36

ዝነኛዋ ቱኒዚያዊት ጦማሪ ሊና ቤን ማሄኒ በ36 ዓመቷ ከዚህ ዓመቷ ነው በሞት የተለየችው።

ሊና የአረብ አብዮትን በዝርዝር መዘገቧ በብዙዎች ዘንድ ዝነኛ አድርጓት ነበር።

ለረዥም ዓመታት ምንነቱ ባልተጠቀሰ ህመም ስትሰቃይ መቆየቷ የተነገረ ሲሆን ዛሬ ጠዋት የህልፈቷ ዜና ተሰምቷል።

የአረብ አብዮት ከመቀስቀሱ በፊት ሊና ወደ ቱኒዚያ ገጠራማ እና የድሆች መንደር በማቅናት የዜጎች ትክክለኛ የኑሮ ገጽታን ለአንባቢዎች ስታቀርብ ቆይታለች።

ሊና ቤን ማሄኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images