የኔልሰን ማንዴላ ሴት ልጅ ዚንዲዚ ማንዴላ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚደንት ኔልሰን ማንዴላ እና የፀረ አፓርታይድ ተሟጋቿ ዊኒ ማዲኪዜላ ማንዴላ ሴት ልጅ የሆኑት ዚንዲዚ ማንዴላ በ59 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
ዚንዲዚ ሰኞ ጠዋት በጆሃንስበርግ ሆስፒታል ሕይወታቸው እንዳለፈ የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።
ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስም በዴንማርክ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።
ዚንዲዚ በዴንማርክ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ከአምስት ዓመታት በፊት ሲሆን በላይቤሪያ ሞንሮቪያ ደግሞ ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል።
በምን ምክንያት እንደሞቱ ግን የተገለፀ ነገር የለም።
ዚንዲዚ የኔልሰን ማንዴላ ስድስተኛ ልጅ ሲሆኑ፤ ከሁለተኛ ባለቤታቸው ከዊኒ ማዲኪዜላ የወለዷት ሁለተኛ ልጃቸው ነበሩ።
ዚንዲዚ ዓለም አቀፍ እውቅናን ያገኙት በአውሮፓውያኑ 1985 ሲሆን የወቅቱ ነጭ መንግሥታት ኔልሰን ማንዴላ የሚደረጉ የትግል እንቅስቃሴዎችን ካወገዙ ከእስር እንደሚለቀቁ የሰጧቸውን እድል ውድቅ ያደረጉበትን ደብዳቤ በአደባባይ ካነበቡ በኋላ ነበር።
ዚንዲዚ በደቡብ አፍሪካ የመሬት ተጠቃሚነት ማሻሻያ ላይ ድምፃቸውን በማሰማትም ይታወቁ ነበር።
ሕልፈታቸውን አስመልክቶ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ በሰጡት መግለጫ ላይ ዚንዲዚ "በትግላችን ወቅት ኢ- ሰብዓዊ የሆነው የአፓርታይድ አገዛዝ ሥርዓት በመታገልና ለነፃነት ትግላችን የማይናወጥ መፍትሔ ያመጡ ሴት ናቸው" ሲሉ ገልፀዋቸዋል።
የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስተር ናሌዲ ፓንዶር በበኩላቸው፤ "ዚንዲዚ የሚታወሱት የነፃነት ታጋያችን ልጅ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ለመብታቸው የቆሙ ጀግና ሴት በመሆናቸውም ጭምር ነው" ብለዋል።
ዚንዲዚ ያደጉት በፀረ አፓርታይድ ትግል ወቅት ሲሆን በወቅቱ አባታቸው በሮበን ደሴት በእስር ላይ ነበሩ። በወቅቱም ቤተሰቡ በአፓርታይድ አገዛዝ ሥርዓት ከፍተኛ በደል ይደርስባቸው እንደነበር ይነገራል።
ከኔልሰን ማንዴላ ስድስት ልጆች በሕይወት ያሉት ሁለት ብቻ ናቸው።












