የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይ አረፉ

የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ዳንኤል አራፕሞይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከኬንያ ነጻነት በኋላ ሁለተኛው ፕሬዝዳንት ሆነው ከሃያ ዓመታት በላይ በብቸኝነት አገሪቱን የመሩት ዳልኤል አራፕ ሞይ በ95 ዓመታችው አረፉ።

ፕሬዝዳንት አራፕ ሞይ የምሥራቅ አፍሪካዋን አገር ኬንያን በበላይነት ለ24 ዓመታት የመሩ ሲሆን፤ አገሪቱ ከእንግሊዝ ነጻነቷን ካገኘች በኋላ ስልጣን የያዙ ሁለተኛው ፕሬዝዳንት ነበሩ።

በሥልጣን ላይ በነበሩበትም ወቅት ሃገሪቷን በጠንካራ ክንዳቸው ገዝተዋል የሚባሉት ዳንኤል አራፕሞይ፤ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚተቿቸው አሉ።

ሞይ ኬንያን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በብቸኝነት ሲመሩ ቆይተው በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት ነበር እንደ ጎርጎሳውያኑ 1992 ሌሎች ፓርቲዎች ወደ ምርጫው መድረክ እንዲመጡ የፈቀዱት።

በስልጣን ዘመናቸው ሙስና፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ግርፋትን ሰቆቃን በመፈጸም ቢወቀሱም በርካታ የሃገሬው ሰው ደግሞ በፍቅር ማሸነፍ ችለዋል ይባልላቸዋል።

ሞይ ስልጣንን በማን አለብኝነት ይዞ በመቆየትና በጨቋኝነት ስማቸው ቢነሳም በዙሪያቸው በሚገኙ የጎረቤት ሃገራት አንዣቦ የነበረውን ጦርነት ወደ ሰላም በመቀየር ግን የተሻለ ሥራ መስራታቸው ይነገርላቸዋል።

ዳንኤል አራፕ ሞይ

የመጀመሪያው የኬንያ ፕሬዝዳንት ጀሞ ኬንያታ መሞታቸውን ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጡት አራፕ ሞይ በመጀመሪያዎቹ የስልጣን ዘመናቸውም 'ፈለግ' የሚለውን ቃል በሚተካው ስዋሂሊ "ንያዮ" መፈክር በርካታ ተከታዮችን አፍርተዋል።

አገሪቱንም አሁን ወዳለችበት የዕድገት ደረጃ እንድትገባ መንገድ ማስጀመር እንደቻሉ ይነገራል።

ነገር ግን በጎርጎሳውያኑ 1982 የተደረገባቸው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በአንድ ጊዜ ወደ አምባገነንነት ቀይሯቸዋል። በዚህም ሳቢያ በርካቶች ወደ እስር ቤት እንዲወረወሩ ሆነዋል። በተጨማሪም የጎሳ ግጭት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ግድያዎች ተፈጸሙ።

'ፈለግ' የሚለው መፈክር ለሀገር ፍቅር ጥሪ ተደርጎ ቢቀነቀንም በኋላ ግን ግርፋት፣ የንጹሃን መታሰር፣ የመንግሥት ተቃዋሚዎችን መግደልና ያለፍርድ ማሰር የስልጣን ዘመናቸው መገለጫዎች ወደመሆን ተቀየረ።

በ1990 ሞይ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው ነበር። በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተደረገባቸው ማዕቀብ፣ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲን እንዲያሰፍኑና የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸውን እንዲገድቡ ጫናዎች ተደርገውባዋል።