አዲሱን የየመን ካቢኔ አባላት የያዘ አውሮፕላን ሲያርፍ በተፈጸመ ጥቃት 22 ሰዎች ተገደሉ

በደቡባዊ የመን ኤደን አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በተሰነዘረ ጥቃት ቢያንስ 22 ሰዎች ሲሞቱ ከ50 በላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በደቡባዊ የመን ኤደን አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በተሰነዘረ ጥቃት ቢያንስ 22 ሰዎች ሲሞቱ ከ50 በላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

አዲስ የተመሠረተውን የየመን ካቢኔ ባለሥልጣናት የያዘ አውሮፕላን ከሳዑዲ ወደ የመን ሲመለስ ነው ፍንዳታው የተከሰተው።

የመንግሥት ባለሥልጣኖች እና እርዳታ ሰጪዎች ጉዳት የደረሰበቸው ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚንስትሩና የካቢኔ አባላቱ ግን እንዳልተጎዱ ተገልጿል። የመረጃ ሚንስትሩ ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረጉት የሁቲ አማጽያንን ነው።

ከ2015 ወዲህ የመን በግጭት እየተናጠች የምትገኝ ሲሆን በሳዑዲ የሚመራ የአረብ አገራት ጥምር ኃይል የሁቲ አማጽያንን አሸንፎ ፕሬዘዳንት አብድራቡህ መንሱር ሀዲን ወደ ሥልጣን መመለስ ይፈልጋል።

በግጭቱ ሳቢያ ከ110,000 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከዓለም የከፋው ሰብአዊ ቀውስ በተከሰተባት የመን፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ለረሀብ ተጋልጠዋል። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ደግሞ ነገሮችን የበለጠ አባብሷል።

አዲሱን የየመን ካቢኔ ወደ የመን የወሰደው አውሮፕላን ካረፈ በኋላ ተሳፋሪዎቹ እየወረዱ ሳለ ከፍተኛ ፍንዳታ ተከስቷል።

ሚንስትሮቹን ለመቀበል አውሮፕላን ማረፊያ የተገኙ ሰዎችም ፍንዳታውን ሽሽት ሲበታተኑ ታይተዋል። ብዙም ሳይቆይ መሣሪያ ሲተኮስ ነበር።

የኤኤፍፒ ጋዜጠኛና የዓለም አቀፍ ትብብር ሚንስትሩ ናጂብ አልአውጅ ቢያንስ ሁለት ፍንዳታ እንደሰሙ ተናግረዋል።

የጥቃቱ መነሻ ገና ባይታወቅም የሮይተርስ የደህንነት ምንጭ ሦስት መሣሪያ በአውሮፕላን ማረፊያው እንደተገኘ ጠቁመዋል። የሳዑዲው አል-ሀዲት የቴሌቭዥን ጣቢያ ሚሳኤል ተተኩሶ ፍንዳታ ሲከሰት የሚያሳይ ቪድዮ ለቋል።

እአአ በነሐሴ 2019 ኤደን ውስጥ ወታደራዊ ትእይንት ሲቀርብ በሁቲ የሚሳኤል ጥቃት ሳቢያ 36 ሰዎች ተገድለው ነበር።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በተሰነዘረው ጥቃት አንድ አባሉ መገደሉን፣ ሦስት አባላቱ መጎዳታቸውንና ሌሎች ሁለት ድጋፍ ሰጪዎች የት እንደደረሱ እንደማያውቅ ይፋ አድርጓል።

የየመኑ አል-ማስዳር ድረ ገጽ እንዳለው፤ የሠራተኞች ሚንስቴር ጸሐፊ ያስሚን አል-አዋዲ፣ የወጣቶችና ስፖርት ምክትል ሚንስትር ሙነር አል-ዋጄህ፣ ምክትል የትራንስፖርት ሚንስትር ናስር ሸሪፍ ከተጎዱት መካከል ይጠቀሳሉ።

ከጥቃቱ በኋላ ጠቅላይ ሚንስትር ማን አብዱልማሊክ እና የካቢኔ አባላቱ ደህንነቱ ወደተጠበቀ ስፍራ ተዘዋውረዋል።

“ሁላችንም ደህና ነን። አውሮፕላን ማረፊያው ላይ የተሰነዘረው የሽብር ጥቃት በየመንና በሕዝቧ የተቃጣው ጦርነት አካል ነው። ኃላፊነታችንን እንድንወጣ የሚያበረታታ ነው” ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ልዑክ ማርቲክ ግሪፍትስ በበኩላቸው ጥቃቱን በጽኑ አውግዘዋል።

“የካቢኔ አባላቱ ከዚህ በኋላም ከባድ ጊዜ ይጠብቃቸዋል። ብርታቱን ይስጣቸው። ይህ ጥቃት የመንን በአፋጣኝ ሰላማዊ ማድረግ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው የሚጠቁም ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ከኤደኑ የአውሮፕላን ማረፊያ ጥቃት በኋላ ጠቅላይ ሚንስትሩ በነበሩበት የፕሬዘዳንት ቤተ መንግሥት አካባቢም ፍንዳታ ነበር። ሳዑዲ የምታስተዳድረው አል አረቢያ የቴሌቭዥን ጣቢያ ፈንጂ የጫነ ድሮን ተተኩሶበት መውደቁን ዘግቧል።

የየመኑ አዲሱ ካቢኔ “የአንድነት ካቢኔ” ይባላል። ውጣ ውረድ ሊገጥመው እንደሚችልም ተጠባቂ ነው። ሆኖም ግን እንዲህ ያለ ጥቃት ይሰነዘራል ተብሎ አልተገመተም።

በደቡባዊ የመን የሚኖሩ ዜጎች ለዓመታት ያለፉበትን ስቃይ የሚቀርፍ አስተዳደር እንደተሾመ ለመጠቆም አውሮፕላን ማረፊያው በቀይ ምንጣፍ ተውቦ ነበር። ሆኖም ግን ጥቃቱ የነገሮችን አቅጣጫ ለውጧል።