የአውሮፓ ሕብረትና ዩናይትድ ኪንግደም በአዲሱ ዓመት በይፋ ተለያዩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መግባቱን ተከትሎ ዩናይትድ ኪንግደም ከአውሮፓ ሕብረት ጋር የነበራትን ግንኙነት በይፋ አቋርጣለች።
ዩናይትድ ኪንግድም (ዩኬ)፤ ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ በጂኤምቲ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 5 ሰዓት [በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ደግሞ ከሌሊቱ 8 ሰዓት] ጀምሮ የአውሮፓ ሕብረት ሕግጋትን መከተል አቁማለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ዩኬ "ነፃነቷን በእጇ" ይዛለች ሲሉ ተደምጠዋል።
አሁን ነገሮችን "በተለይ መልኩና በተሻቀለ ሁኔታ" ማከናወን እንችላለን ሲሉም አክለዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ ዩናይትድ ኪንግደም "የሕብረቱ አጋር እና ጓደኛ ሆና ትቀጥላለች" ብለዋል።
የዩኬ ሚኒስትሮች በሚቀጥሉት ሳምንታት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለውጦች ተግባራዊ ስለሚደረጉ ሕዝቡ አዳዲስ ነገር እንዲጠብቅ አሳስበዋል።
በዩኬና በአውሮፓ ሕብረት አገራት ድንበር አካባቢ መጉላላት ሊኖር ይችላል የሚል ፍራቻ ቢኖርም ባለሥልጣናት ግን አስፈላጊው ሥርዓት ተዘርግቷል ይላሉ።
የዩናይትድ ኪንግደም ሕዝብ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያለን ግንኙነት ይብቃን ሲል በሕዝበ ውሳኔ ፍላጎቱን ያሳወቀው በፈረንጆቹ 2016 ነበር።
ነገር ግን 'ብሬግዚት' በተሰኘ ቅጥያ ስሙ የሚታወቀው ይህ ሂደት ከሦስት ዓመታት ውይይት በኋላ ተግባራዊ ሆኗል።
ላለፉት 11 ወራት ሁለቱ አካላት እየተወያዩ ባሉበት ወቅት ዩኬ ለሕብረቱ የንግድ ሕግጋት ተገዢ መሆን ነበረባት።
አሁን ዩናይትድ ኪንግደም 27 አገራት ካሉበት የአውሮፓ ሕብረት ሙሉ በሙሉ ወጥታለች።
ሕብረቱና ዩኬ ከዓመታት ውይይትና ክርክር በኋላ ዘላቂ መፍትሄ ያመጣል የተባለለትን ስምምነት የፈረሙት ባለፈው ሳምንት የፈረንጆቹ ገና ዋዜማ ነው።
በደረሱት ስምምነት መሠረት የዩናይትድ ኪንግደም አምራቾች ወደ ሕብረቱ ገበያ ከታሪፍ ነፃ መግባት ይችላሉ። ይህም ማለት በሕብረቱ አገራትና በዩኬ መካከል የሚጓጓዙ ዕቃዎች ቀረጥ አይጣልባቸውም ማለት ነው።
ቢሆንም በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚጓዝ ሰው እንደዚህ ቀደሙ ብዙም ሂደት የሌለበት ጉዞ ማድረግ አይችልም።
በስምምነቱ መሠረት ከወዲህ ወዲያ የሚጓጓዙ ሰዎች አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ማሟላት አለባቸው።
ዩኬና ሕብረቱ እስካሁን ድረስ ስምምነት ላይ መድረስ ያልቻሉትና ባንክና ሌሎች አገልግሎቶች እንዴት ይሆናሉ በሚለው ጉዳይ ነው።
ዩኬ ከአውሮፓ ሕብረት መውጣት አልነረባትም የሚሉ ሰዎች አሁንም አሉ።
ከእነዚህ መካከል አንዷ የስኮትላንድ ቀዳሚ ሚኒስትሯ ኒኮላ ስተርጂን ናቸው። ሚኒስትሯ ስኮትላንድን መልሰው የአውሮፓ ሕብረት አባል ለማድረግ በትዊተር ገፃቸው በለጠፉት መልዕክት ቃል ገብተዋል።
የአየርላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው ዩኬ ከአውሮፓ ሕብረት መውጣቷ "በደስታ እልል ልንልለት የሚገባ ጉዳይ አይደለም" ብለዋል።












