ዓይነ ስውሩ የሕግ ተመራቂ ስለምን ራሱን በእሳት አቃጠለ?

የፎቶው ባለመብት, FAMILY
የዛሬ ሳምንት አርብ ታኅሳስ 16/2013 ዓ.ም አንድ ዓይነ ሥውር የሕግ ተማሪ ራሱን በእሳት አቃጥሎ በደረሰበት ከባድ ጉዳት ህክምና ላይ ሳለ ህይወቱ ማለፉ ተሰምቷል።
አብርሃም ዱሬሳ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ዲግሪውን እንዳገኘ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት የመውጫ ፈተና በመውሰድ ላይ እንደነበር ጓደኛው ጣሰው ሃብታሙ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ፈተናው ባለፈው ዓመት በ2012 ዓ.ም ይሰጥ የነበረ ቢሆንም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት በመራዘሙ ለረጅም ጊዜ ለፈተናው ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ያስታውሳል።
ከአብርሃም ጋር በአንድ ግቢ ውስጥ ተከራይተው መኖር ከጀመሩ አምስት ዓመት እንደሆናቸው የሚያስታውሰው ጣሰው፣ ሲዘጋጅበት የነበረውን የመውጫ ፈተና ማክሰኞ ዕለት መውሰድ መጀመሩን ይናገራል።
የመውጫ ፈተናውን ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ፣ ረቡዕ እና ሐሙስ በሰላም ተፈትኖ እንደነበር የሚናገረው ጣሰው ደስተኛም እንደነበር ለቢቢሲ ያስረዳል።
የመጨረሻው የፈተና ዕለት፣ ማለትም አርብ፣ ረፍዶበት ስለነበር የመፈተኛ ኮዱን [የመለያ ቁጥሩን] ረስቶ በችኮላ ፈተናው ወደ ሚሰጥበት ወደ ስድስት ኪሎ ግቢ መሄዱን ያስታውሳል።
ፈተናው የሚሰጠው ስድስት ኪሎ ኤፍ ቢ ተብሎ በሚታወቀው ካምፓስ ስለነበር ወደ ውስጥ ዘልቆ መፈተኛ ኮዱን መርሳቱን እና ይፈትኑት እንደሆነ ቢጠይቅም፣ "ያለእርሱ አይሆንም፣ ሄደህ አምጣ" በመባሉ ወደ ቤቱ መመለሱን ጓደኛው ጣሰው ያስረዳል።
ካለመፈተኛ ኮዱ መግባት ስለማይችል ወደ ቤቱ ሽሮ ሜዳ ተመልሶ፣ ከትራንስፖርት ከወረደ በኋላ ወደ ቤቱ የሚያቀናውን የእግር መንገድን አቋርጦ፣ የመፈተኛ ኮዱን በመያዝ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ሲደርስ ፈተናው መሰጠት ከጀመረ የተወሰኑ ደቂቃዎች ማለፉን ጣሰው ለቢቢሲ ተናግሯል።
"ፈተናው አላለቀም ተማሪዎች አልወጡም ቢያንስ ከ20 ደቂቃ በላይ ይቀር ነበር" ብሎኛል ሲል የሟች አብርሃም የቅርብ ወዳጅ ጣሰው ለቢቢሲ የነበረውን ሁኔቴ አስረድቷል።
የፈተና ተቆጣጣሪዎችን ለማሳመን እና ልባቸውን ለማራራት ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም የሚለው ጣሰው፤ ነገር ግን ምንም ፍሬ እንዳላፈራለት ይናገራል።
"መግባት እንደማይችል ሲነግረው ስላረፈደበት ምክንያት ሊያስረዳ ቢሞክርም፤ "በቀረችው 20 ደቂቃ አብቃቅቼ እሰራለሁ" እያለ ዓይነ ስውር መሆኑን ታሳቢ አድርገው እንዲተባበሩት ቢለምንም፣ ቢያለቅስም፣ ፈተናውን እንዲወስድ ግን አልተፈቀደለትም።"
የሟች አብርሃም ጓደኛ ጣሰው፣ ፈተናውን መፈተን ባለመቻሉ ሲያለቅስ፣ ሲበሳጭ መዋሉን ያስታውሳል።
ጓደኞቹ ሊያጽናኑት ቢሞክርም "በቃ የእድሌ መጨረሻ ነው፣ ዓይነ ስውር ካልተማረ ውጤታማ አይሆንም" እያለ ያለቅስ እነደነበር ይናገራል።
ምሽት ላይ ወደ ቤቱ ሲገባ ወዳጆቹ የመሰላቸው እረፍት ሊያደርግ ቢሆንም፣ እርሱ ግን ቤቱን ዘግቶ፣ በራሱ ላይ ጋዝ አርከፍክፎ፣ በዙሪያዎቹ ተቀጣጣይ ነገር በማኖር ራሱ ላይ እሳት መለኮሱን ጣሰው ገልጿል።
ግቢ ውስጥ ያሉ ሰዎች ተረባርበው የቤቱን በር በመገንጠል እሳቱን አጥፍተው፣ ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ተወስዶ ሕክምና ቢያገኝም ቃጠሎው ከፍተኛ ስለነበር ቅዳሜ ማለዳ 3፡00 ላይ ህይወቱ አልፋለች።
የአብርሃም ቤተሰብ
አብርሃም ዱሬሳ ባለትዳር ሲሆን ባለቤቱ ነፍሰጡር በመሆኗ መስከረም ወር ላይ ለመውለድ ትግራይ ወደ ሚገኙት ቤተሰቦቿ መሄዷን ጓደኛው ጣሰው ለቢቢሲ ተናግሯል።
አብርሃም ብቻውን ለመኖር የተገደደው በተፈጠረው ችግር ምክንያት በረራ ተቋርጦ ስለነበር ባለቤቱ ልጃቸውን ክርስትና አስነስታ መምጣት ስላልቻለች በመዘግየቷ ነበር።
"ለብቻው የሆነው ለዚህ ነው እንጂ ከሚስቱ ጋር ነበር የሚኖረው" የሚለው ጣሰው በጓደኛው ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ይገልጻል።
በየካቲት 12 ሆስፒታል አብረውት የነበሩት አቶ አሸብር ገብረ ሕይወትም ቅዳሜ ዕለት ሆስፒታል ሲደርሱ አብርሃም ነፍሱ እንደነበረችና ሙሉ በሙሉ በእሳት ተቃጥሎ ማየታቸውን ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ማኅበር ፕሬዚደንት አቶ ወሰን አለሙ፣ በማኅበሩ ሦስት ዓመታትን አንዳገለገሉ ገልፀው፤ ከዚህ ቀደም በድሬደዋ ከተማ ከኮቪድ-19 የጥንቃቄ እርምጃዎች የተሳሳተ ግንዛቤ ጋር በተያያዘ አንድ ዓይነ ስውር በተመሳሳይ ሁኔታ ራሱን አቃጥሎ መሞቱን ያስታውሳሉ።
አቶ ወሰን፣ "በአብርሃም ዱሬሳ አርፍዶ በመምጣቱ ወደ ፈተና ክፍል መግባት አትችልም መባሉ ሕግን ካለማወቅ የመጣ ነው" ይላሉ።
"የዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ኮንቬንሽን ተመጣጣኝ ሁኔታን ማመቻቸት ይላል" በማለትም ይህ ማለት የሰዓት፣ የቦታ ማስተካከያ ማድረግ ሊሆን እንደሚችል ያብራራሉ።
አብርሃም ቀደም ባሉት ሦስት የፈተና ቀናት በሰዓቱ ተገኝቶ መፈተኑን ከግንዛቤ በማስገባት፣ ያለ ኮድ ማስተናገድንም ሊያካትት እንደሚችል ያስረዳሉ።
"ይህ በግልጽ ስህተት ነው" የሚሉት ፕሬዝዳንቱ "ፈተናውን የሚያከናውነው አካል እንዲህ አይነት ሥርዓቶችን መዘርጋት ነበረበት" ብለዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ በተማሪ አብርሃም ዱሬሳ ላይ የተፈጸመዉ ክልከላ "ሰብአዊነት የጎደለዉ በመሆኑ መንግሥት ክትትል አድርጎ እርምጃ እንዲወስድ" ሲል ጠይቋል።
ቢቢሲ ስለጉዳዩ ተጨማሪ መረጃን ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ቢደውልም ጉዳዩ እነርሱን እንደማይመለከት ገልፀዋል።
በተጨማሪም ይመለከተዋል የተባለው የፈተናዎች ኤጀንሲም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።












