በአሜሪካ ታሪክ ‘እጅግ ክፉ’ የተባለው ገዳይ ሞተ

ሳሙኤል ሊትል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኤፍቢአይ በአሜሪካ ታሪክ ‘እጅግ የከፋው’ ያለውና ብዙ ሰዎችን የገደለው ሳሙኤል ሊትል የተባለው ግለሰብ በ80 ዓመቱ ሞተ።

ግለሰቡ ካሊፎርያ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እየተደረገለት ሳለ ነው ሕይወቱ ያለፈው። ሳሙኤል 3 ሴቶችን በመግደል የእድሜ ልጅ እስራት ተፈርዶበት ነበር።

ሊሞት ሲቃረብ ግን እአአ ከ1970 እስከ 2005 ድረስ 93 ሴቶችን መግደሉን አምኗል። ሳሙኤል በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩና አደንዛዥ እጽ ተጠቃሚ ሴቶች ላይ ጥቃት ይፈጽም እንደነበር ተገልጿል።

የቀድሞው ቦክሰኛ ሳሙኤል ሰዎችን በቡጢ መቶ ከዘረረ በኋላ አንቆ ይገድላቸዋል። ሟቾቹ ሰውነት ላይ የስለት የመወጋት ወይም በጥይት የመመታት ምልክት ስለማይገኝ በሰው እጅ መገደላቸውን ለማወቅ ያዳግት ነበር።

አብዛኞቹ የገደላቸው ሰዎች አደንዛዥ እጽ ከመጠን በላይ እንደወሰዱ ወይም ድንገተኛ አደጋ እንደደረሰባቸው ስለሚገመት ሞታቸው በፖሊስ ሳይመረመር ቀርቷል።

ከገደላቸው ሰዎች መካከል አስክሬናቸው ያልተገኘ እንዳሉም ኤፍቢአይ ገልጿል።

ማረሚያ ቤት ሳለ የገደላቸውን ሰዎች ሥዕል ለፖሊስ የሰጠ ሲሆን፤ ማንነታቸውን ለማወቅ ሥዕላቸው ይፋ ተደርጓል።

2012 ላይ ከአደንዛዥ እጽ ጋር በተያያዘ ኬንታኪ ውስጥ ታስሮ ለካሊፎርንያ ተላልፎ ተሰጥቷል። ከዚያም የዘረ መል ምርመራ ተደርጎበታል።

የዘረ መል ምርመራው እአአ ከ1987 እስከ 1989 ሎስ አንጀለስ ውስጥ በተከሰቱ ግድያዎች እጁ እንዳለበት ጠቁመዋል።

በመላው አሜሪካ ከመድፈር እስከ ዝርፊያ ድረስ በብዙ ወንጀሎች ተጠያቂ ነው። ጥፋተኛ አይደለሁም ሲል የእምነት ክህደት ቃሉን ቢሰጥም የማይሻር ሦስት የእድሜ ልክ እስራት ግን ተፈርዶበት ነበር።