ኮሮናቫይረስ ፡ የካናዳው ሚኒስትር በኮቪድ-19 ወቅት ሽርሽር በመሄዳቸው ምክንያት ሥልጣናቸውን ለቀቁ

ሮድ ፊሊፕስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሮድ ፊሊፕስ

የካናዳዋ ኦንታሪዮ ግዛት የገንዘብ ሚኒስትር የሆኑት ግለሰብ በኮቪድ-19 ወቅት ለመዝናናት ወደ ካሪቢያን በመጓዛቸው ምክንያት ሥራ ለቀዋል።

የግዛቲቱ ገዥ ዶግ ፎርድ የገንዘብ ሚኒስትራቸው ሥልጣን እንዲለቁ ያደረጉት ኦንታሪዮ የእንቅስቃሴ ገደብ ላይ እያለች ሽርሽር ብለው በመጓዛቸው ነው።

ሚኒስትር ሮድ ፊሊፕስ ይቅርታ ጠይቀዋል። ጉዟቸውንም "የሞኝ ሥራ" ብለውታል።

የግዛቲቱ አስተዳዳሪ እንዳሉት "የፋይናንስ ሚኒስትሩ ሥልጣን መልቀቃቸው መንግሥታቸው ኃላፊነትን በአግባቡ የማይወጡ ሰዎችን እንደማይምር ማሳያ ነው" ብለዋል።

በካናዳ ብዙ ሕዝብ የሚኖርባት የኦንታሪዬ ግዛት በኮሮናቫይረስ ምክንያት ጠበቅ ያለ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሏ ይታወቃል።

የፕሮግረሲቭ ኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ አባል የሆኑት ሚኒስትር ሴይንት ባርትስ ወደ ተሰኘችው የካሬቢያን ደሴት ለሽርሽር የሄዱት በዚህ በታኅሣስ ወር ነው።

በወቅቱ የኦንታሪዮ የጤና ባለሥልጣናት በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁትሩ በመጨመሩ ምክንያት ነዋሪዎች ከቤታቸው ንቅንቅ እንዳይሉ አዘው ነበር።

ኦንታሪዮ ከቀናት በፊት እንደ አዲስ ጠበቅ ያለ የኮቪድ-19 ሕግ አውጥታለች።

ባለፈው ሐሙስ ብቻ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከገባ በበሽታው የተያዙ ከፍተኛው የተባለው ቁጥር [3328] ተመዝግቧል። 56 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።

እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ከሆነ በካናዳ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ582 ሺህ በላይ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ደግሞ 15 ሺህ 600 ደርሷል።

ሚኒስትሩ ከሽርሽር ሲመለሱ ሥራቸውን ለመቀጠል አስበው የነበረ ቢሆንም የግዛቲቱ አስተዳደር ሥልጣናቸውን ቢለቁ የተሻለ እንደሆነ ነግረዋቸዋል።

"እንምታዩት በጣም ከባድ ስህተት ፈፅሜያለሁ። ተጠያቂ መሆን ደግሞ አለብኝ። መሄድ በሌለብኝ ወቅት ነው የተጓዝኩት። ምንም ምክንያት መደርደር አይጠበቅብኝም" ብለዋል ስልጣናቸውን የለቀቁት ሚኒስትር።

የኦንታሪዮ አስተዳዳሪ ሥልጣን በለቀቁት ሚኒስትር ምትክ ሌላ ሰው በጊዜያዊነት ሾመዋል።