ኮሮናቫይረስ፡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት ያቀዘቀዘው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት

የፎቶው ባለመብት, EPA
የኮሮረናቫይረስ ቫይረስ ወረርሽኝ እንደ አዲስ ማገርሸት መጀመሩን ተከትሎ የዘንድሮው የፈረንጆች አዲስ ዓመት በመላው ዓለም በተለያዩ ገደቦችና የጥንቃቄ እርምጃዎች ውስጥ ተከብሯል።
በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቁትና አዲሱን ዓመት አዲስ የሚያደርጉት የርችት መተኮስ ሥነ ሥርዓቶች እንኳን ከሲድኒ እስከ ኒው ዮርክ ድረስ እንዲሰረዙ ግድ ሆኗል።
በተለይ ደግሞ በአውሮፓ አዲሱን የኮሮረናቫይረስ ስርጭት በመፍራት የአዲሱ ዓመት አከባበር ጸጥ ረጭ ባለ ሁኔታ ተካሂዷል።
ፈረንሳይ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ሰዎች እንዳይሰባሰቡና የበዓል ድግስ እንዳያዘጋጁ ለመከልክል እንዲሁም እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ የሚቆየውን የሰዓት እላፊው ተግባራዊ ለማድረግ 100 ሺህ ወታደሮችን አሰማርታለች።
ወረርሽኙ ከአንድ ዓመት በፊት ከጀመረ ወዲህ እስካሁን ከ1.8 ሚሊየን በላይ ሰዎች በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን ከ81 ሚሊየን በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
በፈረንሳይ በተለይ ደግሞ በከተሞች አካባቢ በርከት ያሉ የደንብ ልብስ የለበሱ የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር እንዲያደርጉ የታዘዙ ሲሆን በአዲስ ዓመት ዋዜማም ሥራቸውን ጀምረዋል። በዋና ከተማዋ ፓሪስ በዋዜማው ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ ምንም አይነት እንቅስቃሴዎች አልታዩም ተብሏል።
ፈረንሳይ እስካሁን ሁለት የእንቅስቃሴ ገደብ ደረጃዎችን አስቀምጣለች። በዚህም መሰረት መጠጥ ቤቶች፣ ምግብ ቤቶችና ባህላዊ መሰብሰቢያዎች በአዲሱ ዓመትም ዝግ እንደሆኑ ነው።
በአዲስ ዓመት መልዕክታቸው ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ክትባቱ ዘግይቷል የሚለውን ወቀሳ ለማስተባበል የሞከሩ ሲሆን በምንም አይነት መልኩ ኢምክንያታዊ መዘግየት አይኖርም ብለዋል።
በእንግሊዝ አዲሱ የኮሮናቫይረስ አይነት በፍጥነት እየተሰራጨ ሲሆን በጣም በተጠቁት አካባቢዎች የሚኖሩ 20 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች በቤታቸው እንዲቆዩ ታዘዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው ዜጎች የተቀመጡትን ሕጎች እንዲያከብሩ አሳስበዋል።
"ይህ ማለት አብረው የሚኖሩ ካልሆነ በስተቀር ሰዎች ከጓደኞችና ቤተሰብ ጋር መገናኘት አይችሉም። ማንኛውም አይነት ቦታ ላይ ደግሞ መሰባሰብ አይፈቀድም'' ሲሉ ተደምጠዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በአዲስ ዓመት ዋዜማ ዕለት የለንደን ጎዳናዎች ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ባዶ ሆነው ታይተዋል። ነገር ግን ዓመታዊው ርችት የመተኮስ ሥነ ሥርዓት ሰዎች ቢያንስ ከቤታቸው ሆነው እንዲያዩት በማሰብ ተካሂዷል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
በጀርመን ደግሞ እስከ ጥር 10/2021 የሚቆይ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል። መንግሥት የርችት ሽያጮቸን ጭምር የከለከለ ሲሆን ሰዎች መሰብሰብ የሚችሉበትን ሁኔታም በጥብቅ መመሪያዎች ከልክሏል።
የአገሪቱ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ባስተላለፉት የአዲስ ዓመት መልዕክት ከዘጠኝ ወራት በኋላ በገዛ ፈቃዳቸው ከስልጣናቸው ለመልቀቅ እንዳሰቡ አስታውቀዋል።
አሜሪካ በተለያዩ ግዛቶቿ እና ከተሞቿ ከበዓሉ በፊት የተለያዩ ገደቦችን አስቀምጣለች። በኒው ዮርክ በታይምስ ስኩዌር የተለመደው የአዲስ ዓመት ሥነ ሥርዓት የማይቀር ሲሆን አካባቢው ግን ለሕዝብ ክፍት እንደማይሆን ተገልጿል።
በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ቁጥራቸው የተወሰነ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችና ወሳኝ የሚባሉ ባለሙያዎች እንደሚገኙ ተገልጿል። በተጨማሪም የእነዚህ ሰዎች ቤተሰቦች ብቻ አብረዋቸው እንደሚገቡ ታውቋል።
እንደ ሳን ፍራንሲስኮ እና ላስ ቬጋስ ባሉ ከተሞች ደግሞ የርችት መተኮስ ሥነ ሥርዓቱ ተሰርዟል።
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አዲሱን ዓመት በማስመልከት በትዊተር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በፍጥነት እየተካሄድ ያለውን የክትባት ሥራ በማድነቅ ''ተአምራዊ ምክምና'' በማለት ሂደቱን አድንቀዋል።
በዚህ ወረርሽኝ ክፉኛ ከተጎዱት መካከል አንዷ የሆነችው አውስትራሊያም ብትሆን አዲሱን ዓመት ቀዝቀዝ ባለ ሁኔታ ነው ያከበረችው። በሲድኒ ርችት የመተኮስ ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደ ቢሆንም አንድም ሰው ግን በቦታው መገኘት አልቻለም።
ቻይና በየዓመቱ በዋና ከተማዋ ቤይጂንግ ይካሄድ የነበረውን የአዲስ ዓመት ሥነ ሥርዓትን ሰርዛለች። ነገር ግን ኮሮናቫይረስ መጀመሪያ የተገኘባት በዉሃን ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በከተማዋ መሀል በመሰባሰብ የአዲሱን ዓመት ዋዜማ አክብረዋል።












