ዝውውር ፡ ፖግባ ወደ ዩቬንቱስ? አሊ ወደ ፒኤስጂ?

ፖግባ ዩናይትድን ለቆ ይሄዳል? አይሄድም?

የዘንድሮው የአውሮፓ ኳስ እረፍት አልባ ነው። የክረምት እረፍት ያላገኘው ይህ ተወዳጅ እግር ኳስ ወደ ጥር ወር የዝውውር መስኮት እያመራ ነው።

የሚደግፉት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለብ ለዋንጫ እየተፎካከረም ይሁን ለአውሮፓ ውድድሮች እየተሰናዳ፤ አሊያም ላለመውረድ እየታገለ፤ የውድድር ዘመኑን እያጋመሰ ይገኛል።

ቀጣዩ ወር ደግሞ ጥር ነው። ክለቦች ተጫዋች አስፈርመው ቀዳዳ የሚሸፍኑበት፤ ካልሆነም ሸጠው ገንዘብ የሚያተርፉበት።

በዚህኛው ዙር መስኮት ስማቸው አብዝቶ እየተነሳ ያሉ የፕሪሚዬር ሊግ ተጫዋቾችን እንዳስሳለን።

ፖል ፖግባ - ማንቸስተር ዩናይትድ [ዕድሜ - 27]

ፈላጊ ክለብ - ዩቬንቱስ

ፖግባ ዩናይትድን ለቅቆ ይሄዳል? አይሄድም? ይሄ የሁል ጊዜ ጥያቄ ነው። የዘንድሮውም የዝውውር መስኮት ያለ ፖግባ የሚያምርበት አይመስልም።

የዓለም ዋንጫ አሸናፊው ፈረንሳዊ ፖል ፖግባ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለዩናይትድ 19 ጊዜ ተሰልፎ ተጫውቷል።

ነገር ግን የተጫዋቹ ወኪል [አወዛጋቢው ሚኖ ራዮላ] ፖግባ በዩናይትድ ቤት ያለው ቆይታ አብቅቶለታል እያለ ነው።

ወኪሉ እንደሚለው ከሆነ ፖግባ በማንችስተር ዩናይትድ ቤት 'ደስተኛ አይደለም'፤ 'ክለብ መቀየርም አለበት' ይላል።

ሜሱት ኦዚል - አርሴናል [ዕድሜ - 32]

ፈላጊ ክቦች - ፌኔርባቼ፣ ዲሲ ዩናይትድ፣ ኤልኤ ጋላክሲ፣ ኢንተር ማያሚ

ኦዚል በአርሴናሉ አሠልጣኝ ማይክል አርቴታ ተፈላጊነት ካጣ ቆይቷል። በእንግሊዝም ሆነ በአውሮፓ ውድድሮች ላይ ከሚሳተፉ የክለቡ ተጫዋቾች ስም ዝርዝር ስሙ ተፍቋል።

በፈረንጆቹ 2014 ከጀርመን ጋር የዓለም ዋንጫ ያነሳው መድፈኛ የአርሴናል ከፍተኛው ተከፋይ ነው።

ነገር ግን በሚቀጥለው ክረምት የውል ፊርማው ይገባደዳል። ተጫዋቹ ከአርሴናል ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ከቻለ ውሉን ቀድሞ ቀዶ ክለቡን ሊለቅ ይችላል እየተባለ ነው።

ዴሊ አሊ - ቶተንሃም [ዕድሜ 24]

ፈላጊ ክለቦች - ፓሪስ ሴይንት ዠርሜይን፣ ኤቨርተን

እንግሊዛዊው አሊ ከቶተንሃም ጋር ይዘልቃል ወይ የሚለው ጉዳዩ ከጊዜ ወደ ጊዜ አጠራጣሪ እየሆነ መጥቷል።

በጆዜ ሞውሪንሆ አስተዳደር ብዙም ተሰላፊነት እያገኘም አይደለም። በያዝነው የፕሪሚዬር ሊግ ውድድር ዘመን አንድ ጊዜ ብቻ ነው መሰለፍ የቻለው።

ፒኤስጂ ባለፈው ክረምት ተጫዋቹን ለማስፈረም ቢሞክርም የክለብ ባለቤት ዳንኤል ሌቪ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

የፈረንሳይ ሊግ ባለድሎቹ በሚቀጥለው ወር ተጫዋቹን ለማስፈረም ድጋሚ ሙከራ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኢሊቪዬር ዥሩድ - ቼልሲ [ዕድሜ - 34]

ፈላጊ ክለቦች - ዌስት ሃም፣ አትሌቲኮ ማድሪድ፣ ማርሴይ

ኢሊቪዬር ዥሩድ ከቼልሲ ጋር ያለው ቆይታ እየተገባደደ ይመስላል። ይህ እውን እየሆነ የመጣው የክለቡ አሠልጣኝ ፍራንክ ላምፓርድ ቲሞ ቬርነርን የመሳሰሉ አጥቂዎች ካስፈረመ በኋላ ነው።

ነገር ግን ነባሩ ፈረንሳዊ አጥቂ በ23 ጨዋታዎች 14 ጎሎች በማስቆጠር አሁንም ወሳኝ መሆኑን አሳይቷል።

ቼልሲ ከሴቪያ ጋር በነበረው የቻምፒዬንስ ሊግ ጨዋታ 4 ጎሎች በማስቆጠር ስሙን ተክሏል። ከዚህ ጨዋታ በኋላ ነው በርካታ ክለቦች ፈላጊ ነን ማለት የጀመሩት።

ከላይ ከተጠቀሱት ተጫዋቾች በተጨማሪ የሊቨርፑሉ ዲቮክ ኦሪጊ በዎልቭስ፣ በኒውካስትልና በሊድስ እየተፈለገ ነው።

ተጫዋቹ በሊቨርፑል ቤት ባስቆጠራቸው ጎሎች ታሪክ ሠርቷል።

ዎልቨርሃምተን ዎንደረርስ ምናልባት ኦሪጊን ሊያስፈርሙ ይችላሉ እየተባለ ነው።

የ22 ዓመቱ የቼልሲው ፊካዮ ቲሞሪም በሊድስ የሚፈለግ ሌላኛው ተጫዋች ነው። ተጫዋቹ ባለፈው ውድድር ዘመን 22 ጊዜ ለቼልሲ ተሰልፎ ቢጫወትም በዚህኛው ግን እምብዛም እየታየ አይደለም።

ሌላኛው ስሙ ከዝውውር መስኮቱ ጋር እየተነሳ ያለው ተጫዋች የዎልቭስ አጥቂ አዳማ ትራዎሬ ነው። የ24 ዓመቱ ስፔናዊ አጥቂ አዳማ፤ ዘንድሮ ወደ ፕሪሚዬር ሊጉ ባደጉት ሊድስ ዩናይትድ ይፈለጋል።

ባለፈው ውድድር ዘመን እጅግ ድንቅ አቋም በማሳየት ለስፔን ብሔራዊ ቡድን መጠራት የቻለው አዳማ፣ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ጎል ማስቆጠር ተስኖታል። ቢሆንም ተፈላጊነቱ አልቀነሰም።

አዳማን ለመሸጥ እየተሰናዱ ያሉት ዎልቭሶች የማንቸስተር ሲቲው ዚንቼንኮን ለማስፈረም ደፋ ቀና እያሉ ነው። ተጫዋቹ ከዎልቭስ በተጨማሪ በሳውዝሃምፕተን፣ ሌይስተርና ዌስት ሃም ይፈለጋል።

የጥር ወር ዝውውር መስኮት በሚቀጥለው ቅዳሜ ተከፍቶ ለአንድ ወር የሚቆይ ይሆናል።