ኮሮናቫይረስ አጣብቂኝ ውስጥ የከተተው የአውሮፓ እግር ኳስ

የአውሮፓ እግር ኳስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሁኑ ሰአት ተቋርጦ የሚገኘው የአውሮፓ እግር ኳስ ከዚህ በኋላ በዝግ ስታዲየሞች እንዲደሚካሄድ ግልጽ ቢሆንም መቼ የሚለው ጥያቄ ግን ምላሽ አላገኘም።

ይህንን ያለው በአውሮፓ የሚገኙ ሊጎችን የሚወክለው ማህበር ነው።

የማህበሩ ምክትል ኃላፊ አልቤርቶ ኮሎምቦ እንዳሉት በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተቋረጠው የአውሮፓ ሊግ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብቷል።

‘’አብዛኛዎቹ የማህበሩ አባል ሊጎች በተለይም የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች እንዲጀመሩ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ነገር ግን እንደ ቤልጂየም ያሉ ጥቂት አገራት ከነጭራሹ የዘንድሮው ውድድር እንዲሰረዝ ሀሳብ አቅርበዋል’’ ብለዋል።

የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አርብ ዕለት የወደፊት እርምጃዎችን በተመለከተ ስብሰባ እንደሚያደርግ የሚጠበቅ ሲሆን ዘጠኝ ጨዋታዎች የሚቀሩት ሊግ መቼ ይቀጥል? የሚለው ዋና ርዕስ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ባለፈው ሳምንት አንዳንድ የጀርመን ክለቦች ወደ ስልጠና መመለሳቸውን ተከትሎ እግር ኳስ ማህበራትና የእግር ኳስ አፍቃሪዎች በተስፋ ተሞልተው ነበር።

አልቤርቶ ኮሎምቦ ግን ዋናው ትኩረታችን መሆን ያለበት ሐምሌ እና ነሀሴ ላይ ጨዋታዎቹን እንዴት ማስቀጠል አለብን የሚለው ላይ ነው፤ ከዛ በፊት ያሉት ወራት ላይ ጨዋታዎችን ማካሄድ የማይታሰብ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

‘’በመጀመሪያ የተጫዋቾች ስልጠና መጀመር አለባቸው። በመቀጠል የጨዋታዎቹ አዘጋጆች የደህንነት ማረጋገጫ ስራዎችን ይሰራሉ። ጨዋታዎቹ በዝግ ስታዲየሞች መከናወናቸው የማይቀር ነገር ነው።‘’

‘’እኛ ሀሳብ እናቀርባለን እንጂ የመጨረሻው ውሳኔ ያለው የአገራቱ መንግስት ላይ ነው። የተጣሉት እገዳዎች እንደተነሱ ጨዋታዎችን ከከፍተኛ ጥንቃቄ ጋር በዝግ ስታዲየም እናከናውናለን።‘’

የጣልያን እግር ኳስ ፌደሬሽን እግር ኳስ ተጫዋቾች ሌላው ቢቀር ልምምዳቸውን መስራት እንዲጀምሩ በማሰብ ከመጪው ግንቦት ወር ጀምሮ ተጫዋቾቹ ላይ የኮሮናቫይረስ ምርምራ ማድረግ እንደሚጀምር አስታውቋል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በበኩሉ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተከሰተውን የሊጎችና ውድድሮች መቋረጥን በተመለከተ በሚቀጥለው ሳምንት ስብሰባ ያደርጋል ተብሏል።

ኮሮና
Banner