የሳዑዲ አረቢያ የሴቶች እግር ኳስ ሊግ ተጀመረ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ተጓትቶ የነበረው የሳዑዲ አረቢያ የሴቶች እግር ኳስ ሊግ ተጀምሯል።
600 እግር ኳስ ተጫዋቾች በ24 ቡድኖች ተከፍለው በሪያድ፣ ጅዳና ዳማም ከተሞች ለቻምፒየንሺፕ ዋንጫ ይፋለማሉ።
ማክሰኞ አመሻሹን የተደረገው የመጀመሪያው ጨዋታ በቴሌቪዥን ባይተላለፍም የሳዑዲ መገናኛ ብዙሃን የሊጉ መጀመር ለሴቶች ተሳትፎ እመርታ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ሳዑዲ፤ ሴቶች ስታድየም ገብተው እግር ኳስ ጨዋታዎችን እንዲመለከቱ የፈቀደችው በፈረንጆቹ 2018 ነበር።
ለዘመናት የሃገሪቱ ባለሥልጣናት ባሕላዊና ኃይማኖታዊ እሴቶችን በማጣቀስ ሴቶች በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዳይሳተፉ ሲከለክሉ ቆይተዋል።
ወግ አጥባቂዎች ሴቶች በስፖርት ጨዋታዎች መሳተፋቸው ወደ ኢ-ሞራላዊነት ይመራል ይላሉ።
በመክፈቻው ቀን የሳዑዲ ሴቶች እግር ኳስ ሊግ ጨዋታዎች በዋና ከተማዋ ሪያድና በቀይ ባህሯ ጅዳ ከተማዋ ተከናውነዋል።
ታይገርስ ጅዳ ቻለንጅን 11 ለባዶ፤ አል ሪያድ ዩናይትድ ናጅድ ሪያዲን 10 ለ 1 ያሸነፉበት ጨዋታ በርካታ ጎሎች የተቆጠሩበት ሆኗል።
አሸናፊዋ ቡድን 500 ሺህ የሳዑዲ ሪያል ወይም 133 ሺህ ዶላር ተሸላሚ ትሆናለች።
የሳዑዲ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሊጉን ያስጀመረው ሴቶች በስፖርትና ሌሎች ማሕበራዊ እንቅስቃሴዎች የጎላ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ነው ብሏል።
አረብ ኒውስ ለሰተኘው ጣቢያ ድምጿን የሰጠችው የ16 ዓመቷ ናጂላ አሕመድ በፈረንጆቹ 2021 ከትምህርት ቤት አልፋ ለሊጉ ቡድን ለመጫወት እንደምትሻ ተናግራለች።
"የዚያኔ 17 ዓመት ይሆነኛል። ለመጫወት ብቁ እሆናለሁ ማለት ነው። ማን እንደሚያቆመኝ አያለሁ።"
በተያያዘ በዓለም የመጀመሪያው የሴቶች የጎልፍ ጨዋታ ሳዑዲ አራቢያ የተካሄደው በዚህ ሳምንት ነው።
የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ተቺዎች ግን ሃገሪቱ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመሰል ክንውኖች እየሸፋፈነች ነው ሲሉ ይተቻሉ።
በርካታ የሴቶች መብት ተሟጋቾች አሁንም በሳዑዲ እሥር ቤቶች ይገኛሉ።












