ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን በአሜሪካ እንዲበር ተፈቀደለት

ቦይንግ 737 ማክስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሁለት አሰቃቂ አደጋዎችን ተከትሎ ከበረራ ታግደው የነበሩት የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች እንደገና እንዲበሩ ፈቃድ አግኝተዋል።

የአሜሪካ ደህንነት ተቆጣጣሪዎች አውሮፕላኖቹን ለበረራ ዝግጁ ናቸው ብለዋቸዋል።

የበርካታ ሰዎች ህይወት የተቀጠፈበት አደጋዎችና ተከትለው የመጡትን ምርመራ ተከትሎ ቀውስ ገብቶ ለነበረው ኩባንያ ውሳኔው ትልቅ እመርታ ነው ተብሏል።

ምርመራዎቹ ቦይንግን ጥፋተኛ አድርገውታል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የአየር መንገድ ዘርፉን ኢንዱስትሪ አከርካሪ መምታቱን ተከትሎ ኩባንያውም ከፍተኛ ኪሳራ ገጥሞታል ተብሏል።

የቆዩት አውሮፕላኖች ዲዛይናቸው ተቀይሮና ተሻሽለው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩም ተገልጿል።

የበረራዎችን ደህንነት የሚቆጣጠረው የአሜሪካው የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር እንዳለው አውሮፕላኖቹ ቢፈቀድላቸውም "በአፋጣኝ መብረር አይችሉም" ብለዋል።

በረራ ከመጀመራቸው በፊት አስተዳደሩ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠ ሲሆን ይህም በአውሮፕላኖቹ የሚገጠሙት ሶፍት ዌር (መተግበሪያና) ሌሎች ለውጦችን ጨምሮ ፓይለቶችም ስልጠና ሊወስዱ ይገባል ብሏል።

አስተዳደሩ እንዳለው በአውሮፕላኖቹ ላይ የተደረገው የዲዛይን ለውጥ "አደጋውን ያስከተለውን ሁኔታ ማስወገድ ችሏል" ብሏል።

የአሜሪካ ፌደራል አቪየሽን ኃላፊ እንዳሉት "በአውሮፕላኖቹ ደህንነት ጉዳይ ላይ ስጋት አይግባችሁ፤ መቶ በመቶ እተማመናለሁ በደህንነታቸው" ብለዋል።

"እንዲህ አይነት አደጋዎች እንዳይከሰቱ ለማድረግ የቻልነውን ሁሉ አድርገናል" በማለት ስቲቭ ዲክሰን ተናግረዋል።

አውሮፕላኖቹ እንዳይበሩ ከተደረጉ ከአመት በኋላ ፍቃድ ቢሰጥም ቤተሰቦቻቸውን ላጡት ገና ከኃዘናቸው አልተላቀቁም።

አሜሪካ ፈቃድ በመስጠት ውሳኔዋን ለመቀልበስ የመጀመሪያ ብትሆንም የአውሮፓ አቪየሽን ባለስልጣናትም ተመሳሳይ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ተቃርበዋል ተብሏል።

አሰቃቂዎቹ አደጋዎ

በኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢንዶኔዥያው ላየን አየር መንገድ አደጋዎች በአምስት ወራት ልዩነት የተከሰቱ ሲሆን ለ346 ሰዎች ህይወት መቀጠፍም ምክንያት ሆነዋል።

ዋናው የችግሩ ምንጭ የተባለው ኤምካስ (ማኑቨሪንግ ካራክተርስቲክስ ኦግመንቴሽን ሲስተም) የተሰኘው የመቆጣጠሪያ ሲስተም ነው።

ይህ ሲስተም አውሮፕላኑን የሞተሩ ክብደትና የተቀመጠበትን ቦታ ምክንያት አድርጎ እንዳይቆምና እንዳያጋድል ያደርገዋል። ይህም አውሮፕላኑ ሽቅብ በሚወጣ ጊዜ የሚያሳየውን ዝማሜ ተከትሎ ሚዛኑን እንዲያስጠብቀው ለማድረግ የተሠራ ነበር።

ነገር ግን የኢንዶኒዢያው ላየን አውሮፕላን ምርመራ ውጤት እንዳመላከተው ይህ ሴንሰር አውሮፕላኑ በአፍጢሙ እንዲደፋ የሚያደርግበት ሁኔታ አለ። ይህም የሚሆነው ሚዛኑን ለመጠበቅ የሚልከው መልዕክት (ሲግናል) እርስበርሱ የሚጣረስ በመሆኑ ነው።

ይህም ከአብራሪዎቹ ቁጥጥር ውጭ የሚሆን ነገር ነው። የተከሰከሰው የኢንዶኒዢያ አየር መንገድ ከ20 ጊዜ በላይ የአውሮፕላኑ አፍንጫ ቁልቁል እንዲያዘምና እንዲምዘገዘግ አድርጎታል።

አሁን ቦይንግ አድሼዋለሁ የሚለው ሶፍትዌር በአውሮፕላኑ አፍንጫ የምትገኘው ሴንሰር እርስበርሱ የሚጣረስ ምልእክት ካስተላለፈ ኤምካስ የተሰኘውን መቆጣጠሪ ራሱን በራሱ እንዲያጠፋ የሚያደርግ ነው።

የአሜሪካ ምክር ቤት ሪፖረት እንደሚያሳየው ቦይንግ የደህንነት ስጋቶችን ችላ በማለት አስፈላጊ የሆኑ የፓይለቶችን ስልጠናና ሌሎች ቁልፍ ነገሮችን ወደ ጎን አድርጎ ምርቶቹን በማጣደፉ ለአደጋዎቹ አስተዋፅኦ አድርጓል ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ የፌደራል አቪየሽን አስተዳደሩም ኃላፊነቱን በሚገባ አልተወጣም በሚል ወቀሳን አትርፏል።

ቦይንግ አውሮፕላኖቹን ለማስቀመጥ በመገደዱም 20 ቢሊዮን ዶላር አጥቷል ተብሏል።