በአፍጋኒስታን በአየር ጥቃት የሚሞቱ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ነው ተባለ

አሜሪካና አጋሮቿ አፍጋኒስታን ውስጥ በሚያደርጉት የአየር ጥቃት የሞቱ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር ባለፉት ሦስት ዓመታት በ330 በመቶ ጨምሯል ሲል አንድ ጥናት ይፋ አደረገ።
በፈረንጆቹ 2019 ብቻ 700 ሰላማዊ ዜጎች በአየር ጥቃቶቹ ተገድለዋል ይላል የብራውን ዩኒቨርሲቲ ጥናት።
በዚሁ ዓመት በየቀኑ ቢያንስ ሁለት ሕፃናት በጦርነቱ ሳቢያ ሕይወታቸው ማለፉትን ዘገባው ያመለክታል።
የአሜሪካው ዩኒቨርሲቲ ይፋ ያደረገው 'ኮስትስ ኦፍ ዋር ፕሮጀክት' ነው ይህን ውጤት ያወጣው።
ጥናቱ እንደሚያትተው አሜሪካ 2001 ላይ የተከሰተውን የመስከረም 11 የሽብር ጥቃትን ተከትሎ ባካሄደችው ወረራ በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል።
አጥኚዎች እንደሚሉት አፍጋኒስታን ውስጥ የነበሩ እግረኛ ወታደሮች በመውጣታቸው ምክንያት አሜሪካ ወደ አየር ጥቃት ተዘዋውራለች።
ነገር ግን አሜሪካ ያካሄደቻቸው የአየር ድብደባዎች የታሊባን አማፂ ቡድን አባላት ወደ ሰላም ድርድር እንደሚጡ አስገድዷል ይላል ጥናቱ።
አሜሪካ ባለፈው ታኅሳስ ከታሊባን ጋር ስምምነት ላይ ከደረሰች በኋላ የአየር ጥቃቶቿን አቁማለች። በአፍጋኒስታን ያሉ እግረኛ ወታደሮችን ቁጥርንም ለመቀነስ ቃል ገብታለች።
እንደ ጥናቱ ከሆነ አሜሪካና ታሊባን ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ የአፍጋኒስታን ጦር በበኩሉ የአየር ጥቃቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።
የአፍጋኒስታን መንግሥት አሁንም ከታሊባን ጋር ስምምነት ላይ አይድረስ እንጂ ድርድር ማድረጉን እንደቀጠለ ነው።
የጥናት ቡድኑ ያወጣው ውጤት እንደሚያሳየው የአፍጋኒስታን አየር ኃይል ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላማዊ ዜጎቹን እየቀጠፈ ነው።
በፈረንጆቹ 2020 የመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ብቻ 86 ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል። አልፎም 103 ሰዎች በአፍጋን መከላከያ ሠራዊት ጥቃት ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ባለፈው ወር ሴቭ ዘ ቺልድረን የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት አንድ ዘገባ ይፋ አድርጎ ነበር።
የዚህ ድርጅት ዘገባ እንደሚያሳየው አፍጋኒስታን ውስጥ ባለፉት 14 ዓመታት በየቀኑ ቢያንስ አምስት ሕፃናት ተገድለዋል አሊያም ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ደግሞ በፈረንጆቹ ከ2005 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት ከ26 ሺህ በላይ ሕፃናት ተገድለዋል ወይም ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።















