አፍጋኒስታን፡ ጠመንጃ አንስታ 'ታሊባኖችን' ያንበረከከችው ትንሽዬ ልጅ ታሪክ

የፎቶው ባለመብት, GHOR DISTRICT GOVERNMENT
ኑሪያ ትባላለች። አፍጋኒስታን ገጠር ውስጥ ነው የምትኖረው።
የሆነ ቀን 'ሙጃሂዲን' ነን የሚሉ ታጣቂዎች ቤቷ መጡ። በማታ ነው ታዲያ።
ሩሲያ ሠራሹን ኤኬ-47 ክላሽ አንስታ አርከፈከፈችባቸው። ሁለቱ ሞቱ፤ ሦስተኛው ክፉኛ ቆሰለ።
የአፍጋኒስታን ማዕከላዊ መንግሥት በሄሊኮፕተር ካለችበት ወዲያውኑ አሳፍሮ ወዳልታወቀ ሥፍራ ለደኅንነቷ ሲባል ወሰዳት።
ይቺን 'ጀግና' ሕጻን በቴሌቪዥን እያቀረበ "እንዲህ ነው እንጂ መጀገን" እያለ ነው የካቡል መንግሥት።
ቀስ በቀስ ግን ጥያቄዎች ተነሱ። ኑሪያ ከገደለችው ሙጃሂዲን አንዱ ባሏ እንደሆነ ተደረሰበት። ያን ምሽት በትክክል ምንድነው የሆነው?
ኑሪያ በእርግጥ ጀግና ናት? ወይስ የአፍጋኒስታን መንግሥት ታሊባኖችን ለማንቋሸሽ እየተጠመባት ነው?
"ባሏ ከቤተሰብ ጋር ጸብ ላይ ነበር"
ድቅድቅ ጨለማ ነበር፤ ራሳቸውን ሙጃሂዲን ብለው ነው የሚጠሩት። ተፋላሚዎች እንደማለት ነው። የታሊባን ሽምቅ ተዋጊዎች ናቸው።
በሌሊት የመጡት ለ'ዚያራ' አይደለም።
እርግጥ የኑሪያ አባት የአገር ሽማግሌ ናቸው። ለማዕከላዊ መንግሥት ድጋፍ የሚሰጥ የአካባቢው ሽማግሌ። እርሳቸውን አንቀው ሊወስዱ ነበር አመጣጣቸው።
ኑሪያ እንደምትለው የቤቱ በር ልክ ከሌሊቱ 7፡00 ሰዓት ላይ በኃይል ተሰብሮ ተከፈተ።
የ15 ዓመቷ ኑሪያ መኝታ ቤት እንቅልፍ ጥሏት ነበር። ልክ የበሩን መሰበር ስትሰማ እመር ብላ 'ኤኬ-47' ክላሽ አነሳች።
ድምጽዋን አጥፍታ ጠበቀች። መጀመሪያ ወደ አእምሮዋ የመጣው በሦስት ዓመት የሚያንሳትና የምትወደው ታናሽ ወንድሟ ነበር።
እሱም በራሱ መኝታ ቤት ነበር የተኛው።
ትንፋሽዋን ውጣ ማዳመጥ ጀመረች። ሙጃሂዲኖች ወላጆቿን ይዘዋቸው ሲወጡ ይሰማታል። የእነሱ ቤት ገጠር ኮረብታ ላይ ያለ ጎጆ ነው።
ከዚያ በኋላ ምን እንደተከሰተ ኑሪያ ለቢቢሲ እንዲህ አለች።
"ወዲያውኑ አባትና እናቴን ይዘዋቸው እንደወጡ ተኩስ ሰማሁ። ገደሏቸው።"
ኑሪያ ተንደርድራ ወጣች. . .
ያደገችው ታጣቂዎቹ በተደጋጋሚ ጥቃት በሚሰነዝሩበት የገጠሩ ክፍል ነው። እንደ ብዙዎቹ የአፍጋኒስታን ሴት ልጆች ድምጽዋ እንኳ የማይሰማ፣ አይናፋር ናት።
ይህ ማለት ግን መሣሪያ አትታጠቅም ማለት አይደለም። ከበድ ያለ ክላሽ እንዴት በትከሻዋ መሸከም እንዳለባት፣ እንዴት አነጣጥራ ማለምና መተኮስ እንደምትችል ገና ጡት ሳትጥል የተማረች ነው የምትመስለው።
አባቷ ግሩም አድርገው አሰልጥነዋታል።
ኑሪያ ያን ምሽት እናት አባቷ ላይ ጥቃት ሲደርስ በእሷ ዕድሜ ያሉ ሴት ልጆች እንደሚሆኑት ወደ ጓሮ ሄዳ አላለቀሰችም፤ ወይም ደግሞ አልጋ ሥር ገብታ አልተሸሸገችም።
ክላሹን ወድራ ወላጆቿን ወደገደሉት ታሊባኖች ተራመደች። የአባቷን ክላሽ እንዳነገበች ነው። ጥይት እስክትጨርስ ድረስ ባለ በሌለ ኃይሏ አርከፈከፈችባቸው።
ጥይቱ ሲያልቅ ወደቤት ተመልሳ ገባች።
ወደእነሱ ቤት በርከት ብለው የመጡት ታሊባኖች ሽሽት ጀመሩ።
ከጥቂት ሰዓታት በኋላ እንደተደረሰበት ከሆነ ደጅ ላይ የአምስት ሰዎች ሬሳ ተጋድሟል።
ከአምስቱ ሁለቱ አባትና እናቷ ናቸው። ሌላኛው ጎረቤታቸው የነበረ ሰው ሬሳ ነው። ከዚህ ሌላ የሁለት ጥቃት አድራሾች ሬሳ ግን አሁንም እያነጋገረ ነው።
ኑሪያ ለቢቢሲ እንዲህ አለች፣ "ሁሉም ነገር አስቀያሚ ነበር፤ አባቴ አካል ጉዳተኛ ነበር፤ ገደሉት፤ እናቴ ምንም የምታውቀው ነገር አልነበረም፤ እሷንም ገደሏት። ቆይ ግን እማዬ ምን አረገቻቸው?"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአፍጋኒስታን ልጃገረዶች እያመረሩ ይሆን?
በአፍጋኒስታን ሰላም የለም። ብዙዎቹ የአሁን ትውልዶች በበረሃ ተጸንሰው በእርስ በርስ ጦርነት መሀል የተወለዱ ናቸው።
እንደ ኑሪያ ያሉ ሴቶች የሚደርስባቸው የሕይወት መከራ መልከ ብዙ ነው። መዝሙራቸውን የሚያጅበው የጥይት እሩምታ ነው። 'ሰኞ-ማክሰኞ' የሚጫወቱት በቀለሀዎች ነው።
ነጻነት የሚባል ነገር ቅንጦት ሳይሆን ሲጀመርም አያውቁትም። ትምህርት እንደ ጨረቃ ሩቅ ነው። ትልቁ 'ስኬታቸው' ባል ማግባት ነው።
እዚያ ያለው ማኅበረሰብ በወንድ የበላይነት አስተሳሰብ ውስጥ የተነከረው እስከ አንገቱ ነው።
በመንግሥትና በአማጺያኑ ታሊባኖች መካከል ያለው ጦርነት ለዘላለም የሚቀጥል ነው የሚመስለው። ፍልሚያው ሩብ ክፍለ ዘመኑን ደፈነ፤ 25 ዓመት።
የመንግሥት ኃይሎች ካቡልንና ትልልቅ ከተሞችን ይቆጣጠራሉ። ታሊባኖች ጠረፉን፣ ተራራውን፣ ሸንተረሩን፣ ገጠሩን ይቆጣጠራሉ።
እንደ ኑሪያ ያሉ የገጠር ሴቶች ታዲያ በሁለቱ መካከል ይጎተታሉ። ለማን ይታመኑ?
ኑሪያ በምትኖርበት ጎር በሚባለው ገጠር ውስጥ ታሊባኖች ማታ ማታ እየመጡ አንዳንድ የአካባቢውን ሰዎች ገድለው ይመለሳሉ። የኑሪያ ታሏቅ ወንድም ለቢቢሲ እንደተናገረው አባታቸው ጥቃት የደረሰበት ለማዕከላዊው መንግሥት ስለሚያደላ ነው።
የኑሪያ የእንጀራ ወንድም ፖሊስ ሆኖ ይሰራል። የእሱም ደኅንነት ሁሌም አደጋ ላይ ነው። ለነገሩ የሁሉም አፍጋናዊ ሕይወት አደጋ ላይ ነው።

የፎቶው ባለመብት, LOCAL AFGHAN AUTHORITIES
ኑሪያ የገዛ ባሏን ገድላው ይሆን?
በአሥራዎቹ ዕድሜ እኩሌታ ላይ ያለችው ኑሪያ ያን ምሽት ክላሽዋን አንግባ ወላጆቿን የገደሉትን ታጣቂዎች ከተበቀለች በኋላ ዝነኛ ሆናለች።
ሆኖም ቀስ በቀስ እርስበርሳቸው የሚጋጩ መረጃዎች መውጣት ጀመሩ።
ታላቅ ወንድሟ የሚናገረው ሌላ፣ መንግሥት የሚለው ሌላ፣ የአካባቢው ፖሊስ የሚለው ሌላ፣ የታሊባን ሰዎች የሚሉት ሌላ. . .።
ቢቢሲ ከበርካታ ምንጮች ያገኘው መረጃ እንደሚያረጋግጠው ከሆነ ያን ምሽት በክላሽ ግንባር ግንባራቸውን ካለቻቸው ሰዎች መካከል አንዱ የኑሪያ የገዛ ባሏ የነበረው ሰው ሳይሆን አይቀርም።
የተምታታው መረጃ ለመውጣቱ አንዱ ምክንያት በገጠሪቱ አፍጋኒስታን ሴቶች በምን ያህል የከፋ ሁኔታ እንደሚኖሩ ለመደበቅ የተደረገ ሙከራ ይሆናል። እዚያው ሕይወት ትብታቦ ይበዛዋል።
የአፍጋኒስታን ሴቶች በባሎቻቸው የሚደርስባቸው ጭቆና፣ የባህልና የአስተሳሰብ ድጋፍ አለው። ወግ አጥባቂው የአፍጋን ባሕል አባወራዊነት የሚጫነው ነው። ዘመናዊ ትምህርት ሩቅ ነው። አንዳንድ ቦታ እንዲያውም ነውር ነው። ሰው እንዴት ይማራል? ብለው ዘመናዊ ትምህርትን የሚጠሉ ቡድኖች አሉ።
በዚያ ምሽት በትክክል ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ ያላስቻለበት አንዱ ምክንያትም ያን ምሽት ታሊባኖች ለምን እነ ኑሪያ ቤት መጡ ከሚለው ነጥብ ይጀምራል።
ሁሉም ግን በአንድ ነገር ላይ ይስማማሉ። ያን ቀን ቀትር ላይ በዚያች ገጠር ከተማ ጥቃት ተሰንዝሮ እንደነበረና መታኮስ እንደነበረ. . .።
ኑሪያ የምትለው ያን ቀን ሙጃሂዲኖች የመጡት አባቷ ላይ አደጋ ለመጣል ነበር። ታሊባኖች በበኩላቸው ይህን ያስተባብላሉ።
ያን ዕለት ግጭት ተፈጥሮ እንደነበር አምነው ነገር ግን ከዚህች ታዳጊ ዘንድ ምንም እንዳላደረሳቸው፤ ጉዳይም እንዳልነበራቸው፣ ሞትም እንዳልተከሰተ ይከራከራሉ።
"ያን ቀን ኢላማ ያደረግነው የአካባቢው ኬላ ላይ የሚገኙ ፖሊሶችን ነበር። በዚህም ጥቃት ታሊባን ወታደሮቻችን ቆስለዋል እንጂ የሞተብን ሰው የለም" ብለዋል።
የአካባቢው ፖሊስና የአፍጋኒስታን መንግሥት በበኩላቸው ያን ምሽት ታሊባኖች ጥቃት ሊፈጽሙ ሞክረው ድባቅ ተመተዋል ይላል።
ኑሪያንም "ትንሽዋ ጀግኒት" ሲል አመካሽቷል።
ዞሮ ዞሮ ከክስተቱ በኋላ ኑሪያና ታናሽ ወንድሟ ለደኅንነታቸው ወደተዘጋጀላቸው ሥፍራ ከተወሰዱ በኋላ በአፍጋኒታንና በሌሎች አገሮች የሚገኙ ማኅበራዊ ድራምባዎች የኑሪያን ጉዳይ ሲያራግቡት ሰንብተዋል።
በዚያች አገር ዜጎች በታሊባን ላይ ለሚያነሱት ነፍጥ የጀግና ሜዳል ሲሰጣቸው ኑሪያ የመጀመርያዋ አይደለችም። የካቡል መንግሥት በታሊባኖች ላይ ሥነልቡናዊ ጦርነት ለመክፈት ይህን አዘውትሮ ያደርጋል።
ለዚህም ነው አንዳንዶች የፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋኒን አስተዳደር ክፉኛ እያብጠለጠሉት ያሉት።
ይቺን ምንም የማታውቅ አዳጊን ልጅ ለፕሮፓጋንዳ መሣሪያነት መጠቀም ጭካኔ ነው ይላሉ ተቺዎች።
"ምን ታውቃለች ይቺ ልጅ፤ በሁለት ተዋጊ ቡድኖች መካከል ራሷን ያገኘች እድለቢስ ናት፤ እሷን ለፕሮፓጋንዳ ማዋል ደግ ነው ወይ?" የሚሉ ብዙ ናቸው።
ሌሎች ደግሞ "ኑሪያ ጀግና ናት፤ የፈጸመችው ጀብዱ ለዓለም መነገር አለበት፤ ይህን ማድረግ ችግሩ ምን ላይ ነው" ይላሉ።
አንድ ግለሰብ ለምሳሌ በትዊተር ሰሌዳው እንዲህ ጽፏል፣
"ሕዝቧ የርስበርስ ጦርነት ውስጥ ተማግዶ በሚያድግባት አገር፣ የሰላምና የሕይወትን ዋጋ በየቀኑ የሚመለከት ሕዝብ እንዴት አንዲት ልጅ መሣሪያ አንስታ ሰዎችን ረፈረፈች ብሎ መግደልን እንደመልካም ያወድሳል፤ እኔ ግርም ይለኛል።"
ሌላ ግለሰብ ደግሞ እንዲህ ጻፈ፣
"ኑሪያ ለሴቶች ተምሳሌት ናት። የገዛ ሕይወቷን ለመጠበቅ የማንንም ወንድ ድጋፍና ከለላ የማትሻ ሴት!"

ኑሪያ እነማንን ገደለች?
አንድ የአካባቢው ፖሊስ መኮንን "ኑርያ በገደለቻቸው ሰዎች ላይ በተደረገ ማጣራት ሟቾቹ በአካባቢው የሚታወቁ የታሊባን ደጋፊዎች እንደሆኑ ተደርሶበታል ብለዋል" ለቢቢሲ።
ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ የደረሰበትና ኑሪያ ክፉኛ ያቆሰለችው ሦስተኛው ሰው ደግሞ እውቅ የታሊባን ኮማንደር የሆነው ሳይድ ማሱም ካምራን ነው ብሏል ፖሊስ።
ይህ ምን ያህል እውነት ነው የሚለው ከገለልተኛ ወገን አልተጣራም።
የኑሪያ ታናሽ ወንድምና ኑሪያ፣ ፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋኒ በቤተ መንግሥት የጀግና አቀባበል አድርገውላቸዋል።
አወዛጋቢ ነገር የተነሳው ከዚህ በኋላ ነበር።
የጀግና ኒሻን ከተቀበለች ከጥቂት ቀናት በኋላ እሷ ከገደለቻቸው ሰዎች አንዱ የገዛ ባሏ እንደነበር መረጃዎች መውጣት ጀመሩ። ይህ እውነት ነው? ለምን ገደለችው ታዲያ?
የኑሪያ የቅርብ ቤተሰብ አባላት ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ከሟቾቹ አንዱ የኑሪያ ባል ነበር፤ ራሂም ይባላል። ወደዚያ ሰፈር መጥቶ የነበረውም አባትየው ልጃቸውን ለእሱ አሳልፌ አልሰጥም ብለው በመከልከላቸው ነበር።
ቀደም ብሎ በቤተሰቡ መካከልም ግጭት ተከስቶ ነበር። ኑሪያን ያመጧትም ከእሱ ቤት ሲሆን፤ ራሂም ደግሞ ያን ምሽት የመጣው እሷን መልሶ ለመውሰድ ነበር።
ይህን ለማሳካት ደግሞ ባልየው የታሊባን ሚሊሺያዎችን ድጋፍ ሳይጠይቅ አልቀረም። እሱ ራሱ የታሊባን ደጋፊ ነበር የሚሉ መረጃዎችም ወጥተዋል።
ጀግና ተብላ የተወደሰችው ትንሽዋ ኑሪያ ደግሞ ይህንን ታስተባብላለች። "ኧረ ተጋብተን አናውቅም" ነው የምትለው።
ጉዳዩን እናውቃለን የሚሉት ደግሞ ኑሪያ የቅያሪ ጋብቻ ስምምነት ውስጥ ነበረች ይላሉ።
ይህ ምን ማለት ነው ሲባሉ፤ ሁለት የሴት ልጅ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ለትዳር የሚለዋወጡበት ሥርዓት እንደሆነ ያስረዳሉ።
ይህም አፍጋኒስታን ውስጥ የሚፈጸም የተለመደ ድርጊት ነው።
በዚህ የጋብቻ ልውውጥ ስምምነት መሰረት ረሂም ኑሪያን ሁለተኛ ሚስቱ አድርጎ ሲያገባት የኑሪያ አባት ደግሞ የረሂም ዘመድ ከሆኑ ሌሎች ሴቶች ሁለተኛ ሚስት ያገባሉ።
ሆኖም ይህ እንዲሆን የረሂም ዘመዶችም ሆኑ የኑሪያ ዕድሜ ገና ስለሆነ በርከት ያለ ዓመት መጠበቅ ያሻል። ወይም አያሻም።
ቢቢሲ ይህንኑ ለማረጋገጥ ሩቅ በሚባለው ምዕራብ አፍጋኒስታን ውስጥ በሚገኘው ኒምሩዝ አውራጃ የሚኖሩትን የራሂምን እናት አግኝቶ፤ ሟቹ ልጃቸው በእርግጥም ኑሪያን አግብቷት እንደነበር ተናግረዋል፡፡
እናት ሻፊቃ የራሒም እናት ሲሆኑ ስለ ጋብቻው ለቢቢሲ በስልክ እንዳብራሩት ኑሪያ ልጃቸው ረሒምን ያገባቸው ከሦስት ዓመት በፊት ገና የ12 ዓመት ልጃገረድ ሳለች ነበር።
በልዋጩም የኑሪያ አባት የሟች የረሒምን የወንደም ወይም የእህት ሴት ልጆች ሊያገቡ ስምምነት ነበር። ምን ዋጋ አለው ሁለቱም በአንድ ምሽት ወደቁ እንጂ!
ነገር ግን ከሁለት ዓመት በፊት የኑሪያ አባት ድንገት ይህንን ስምምነት አፍርሰውት ልጃቸው ኑሪያን ከረሒም ቤት ወስደዋታል።
ረሒም በዚያ ምሽት ወደዚያ የሄደውም ሚስቱን ኑሪያን ለማስመለስ ነበር ማለት ነው።
"ልጄ እዚያ እነ ኑሪያ ቤት የሄደው አደጋ ለመጣል አልነበረም፤ ለሽምግልና ነበር። እኛ ድሆች ነን፤ እነሱ የሚፈሩ ቤተሰብ ናቸው፤ ልጄ ሽጉጥ በእጁ እንኳን ይዞ አያውቅም" ብለዋል እናትየው ለቢቢሲ።
ልጃቸው የታሊባን አባል ስለመሆኑም አስተባብለዋል።
ያን ምሽት ምን እንደደተፈጠረ በትክክል ማዋቅ ፈታኝ ሆኗል።
ኑሪያና አቻዎቿን በተመለከተ ማለት የሚቻቸው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ እነ ኑርያ በአፍጋኒስታን የወንዶች ዓለም ውስጥ የራሳቸው ሕልውና የሌላቸው የወንድ ሕይወት አድማቂዎች መሆናቸውን።
ሲኖሩ ቀርቶ ሲገድሉም፣ ሲሞቱም እነሱ የእራሳቸው አይደሉም። አባታዊ ዓለም። የወንዶች ዓለም።















