ሁለት ጊዜ በጥይት ተመታ በህይወት የተረፈችው አራስ

የፎቶው ባለመብት, WAKIL KOHSAR
ከአንድ ሳምንት በፊት ታጣቂዎች አፍጋኒስታን ካቡል በሚገኘ አንድ ሆስፒታል ላይ ጥቃት መሰንዘራቸው ይታወሳል።
በወላዶች ክፍል ላይ በተሰነዘረው በዚህ ጥቃት እናቶች፣ ጨቅላ ህጻናት እና ነርሶችን ጨምሮ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 24 የደረሰ ሲሆን በርካቶች መቁሰላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚንስትር ተናግረዋው ነበር።
ከዚህ ጥቃት ቀጥሎ በነበረው ቀንም፤ አንድ የቀብር ሥነ ሥርዓትን ታድመው በነበሩ ሰዎች ላይ አንድ አጥፍቶ ጠፊ እራሱን በቦምብ አጋይቶ ለሌሎች 34 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል።
በፖሊስ አዛዡ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለተፈጸመው ጥቃት አይኤስ ኃላፊነቱን እውስዳለሁ ብሏል።
እስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደ አካል ባልተገኘለት የሆስፒታሉ ጥቃት ከሞቱት በርካታ ሰዎች ባሻገር በርካቶች ሲቆስሉ አንዲት አራስ በሁለት ጥይት ተመትታ ተርፋለች።
እናቶችን ኢላማ ባደረገው በዚህ የካቡል ሆስፒታል ጥቃት 16 ወላዶች ተገድለዋል። ከሟቾቹ መካከል የጨቅላዋ አሚና እናት ትገኝበታለች። ጨቅላዋ አሚና ግን ሁለት ጊዜ በጥይት ብትመታም በህይወት መትረፍ ችላለች።
የአሚና አባት የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውሱ፤ ታጣቂዎች ሆስፒታሉ ላይ ጥቃት መሰንዘር ሲጀምሩ አሚና ገና መወለዷ ነበር።
ታጣቂዎቹ ወደ ሆስፒታሉ ዘልቀው በመግባት እናቶችን ዒላማ አድርገው ሲገድሉ፤ አሚናም ሁለት ጊዜ እግሯ ላይ በጥይት ተመታለች።
ዶክተሮች የአሚናን በህይወት መትረፍ "ታዓምራዊ ነገር ነው'' ሲሉ ይገልጹታል።
"የተኩስ ድምጽ እየተሰማ እያለ ባለቤቴ 'አጥፍቶ ጠፊ ነው?' ስትል ጠየቀችኝ። እንዳትጨነቅ በማሰብ 'አጥፍቶ ጠፊ አይደለም' አልኳትንና እንድትደበቅ ነገሪያት አንዱን ታጣቂ ተከትዬ ወጣሁ።
"ስመለስ አሚናን እንደታቀፈች ተገድላ አገኘኋት" በማለት የጨቅላዋ አባት ራፊኡላ ይናገራል።
ባለቤቱ ልቧ ላይ እና አግሯን በጥይት እንደተመታች የሚናገረው ራፊኡላ፤ አዲስ የተወለደችውን ሴት ልጁን ለማዳን በፍጥነት ህክምና እንድታገኝ ለማድረግ መጣሩን ይናገራል።
"ባለቤቴን እየቀበርኩ እያለሁ ዶክተሮች ደውለው 'የአሚና እግር መቆረጥ አለበት' አሉኝ እኔም 'እባካችሁ እግሯን አትቁረጡ። እናት የሌላት ጨቅላ ናት። የወደፊት ህይቷን አታክብዱባት' አልኳቸው" ይላል።
የተቻላቸውን ለማድረግ ቃል የገቡለት ሃኪሞች ያካሄዱት የቀዶ ህክምና ተሳክቶ የአሚና እግር ሳይቆረጥ ቀርቷል።
በተደረገላት ሁለት ተከታታይ የቀዶ ህክምና አሁን ላይ ሃኪሞች አሚና ከፍ ስትል መራመድ እንደምትችል ተስፋ አድርገዋል።












