በፓኪስታን የተገደሉ ታዳጊ ሴቶችን እየሳመ የተቀረፀው ግለሰብ ተያዘ

በፓኪስታን በክብር ግድያ' የተገደሉ ሴቶችን ለመቃወም የተጠራ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በፓኪስታን በክብር ግድያ' የተገደሉ ሴቶችን ለመቃወም የተጠራ ሰልፍ

በፓኪስታን ሁለት የተገደሉ ታዳጊ ሴቶችን እየሳመ ቪዲዮ የተቀረፀው ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታውቋል።

በፓኪስታንም ሆነ በመካከለኛው ምሥራቅ ባሉ አገራት "ማኅበረሰቡን አዋርደዋል፤ የቤተሰባቸውን ክብር ዝቅ አድርገዋል" ተብለው የሚወነጀሉ ታዳጊ ሴቶች "የክብር ግድያ" (ኦነር ኪሊንግ) ተብሎ በሚጠራው ሁኔታ በቤተሰብ አባላቸው ይገደላሉ።

እነዚህም ታዳጊዎች በቤተሰብ አባላት በጥይት ተተኩሶባቸው ነው የተገደሉት።

ፖሊስ ባወጣው መግለጫ የ28 ዓመቱ ኡማር አያዝ ቪዲዮውን በማዘጋጀት ወንጀል በቁጥጥር ስር አውሎታል። ቪዲዮውንም ሲቀርፅ የነበረውና ቪዲዮውንም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ያጋራውም ሌላኛው ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኛል።

ከዚህም በተጨማሪ የአንደኛዋ ታዳጊ አባትና ሦስት ዘመዶች ግድያውን ሪፖርት ባለማድረግና መረጃን በመደበቅ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ግድያውን የፈፀመው መሐመድ አስላም እየተፈለገ እንደሆነ ፖሊስ አስታውቋል።

የ16 እና የ18 ዓመት ታዳጊዎቹ የአጎት ልጆች ሲሆኑ ግድያው የተፈፀመባቸውም ባለፈው ሳምንት የድንበር ከተማ በሆነችው ሻም ፕሌይን ጋርዮም ግዛት ነው።

የአካባቢው ፖሊስ ኃላፊ ሻፉላህ ጋንዳፑር ለሮይተርስ የዜና ተቋም እንዳሳወቁት ስለ ግድያው ሪፖርት የሰሙት ከማኅበራዊ ሚዲያዎች መሆኑን ነው።

ባለስልጣናቱ ግድያው በተፈፀመበት አካባቢ ተገኝተው ባደረጉት ምርመራ "ደምና፤ በደም የተለወሱ አልባሳት" አግኝተዋል።

ግድያው የተፈፀመው ታዳጊዎቹ ከአንድ ወንድ ጋር ሆነው የሚያሳይ ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መውጣቱን ተከትሎ ነው ተብሏል።

ቪዲዮውን ቢቢሲ እንደተመለከተው ሦስት ታዳጊ ሴቶች ከአንድ ወንድ ጋር ሰው በሌለበት ቦታ ላይ ቪዲዮ ሲቀረፁ የሚያሳይ ነው።

ቪዲዮው የተቀረፀው ባለፈው ዓመት ሲሆን በቅርብ ሳምንታት ነው ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ወጥቶ ነው ብዙዎች የተጋሩት።

ሦስተኛዋ ታዳጊ ያልሞተች ሲሆን፤ የገዳዪም ሚስት ናት ተብሏል። በአሁኑም ሰዓት ተደብቃ እንደምትገኝም ተገልጿል። ፖሊስ በበኩሉ ህይወቷ ስጋት ላይ በመሆኑ እየፈለጓት መሆኑንም አሳውቀዋል።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዋች በፓኪስታን በታዳጊና በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ግድያዎች አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ብሏል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች "የክብር ግድያ" በሚባለው ድርጊት በፓኪስታን በየዓመቱ አንድ ሺህ ሴቶች እንደሚገደሉ ይናገራሉ።

ብዙዎቹ ግድያዎች ሪፖርት የማይደረጉ ሲሆን፤ ከአራት ዓመታት በፊትም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ዝነኛ የሆነችው ኩዋንዲል ባሎሽ መገደል ከፍተኛ ውግዘትን አስከትሏል።

ይህንም ተከትሎ ፓኪስታንን የሚገዛው ወግ አጥባቂው ፓርቲ ህጉን እንዲያጠብቅ አስገድዶታል።

Presentational grey line

የ'ክብር ግድያ' ምንድን ነው?

የክብር ግድያ በቤተሰብ ላይ ውርደትን አስከትለዋል የሚባሉ ሴቶች ላይ በቤተሰብ አባል የሚፈፀም ግድያ ነው።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንዲሁም ሂዩማን ራይትስ ዋች ለግድያው ተብለው ከሚሰጡ ምክንያቶች መካከል ከሰበሰቧቸው መረጃዎች፦

  • ቤተሰብ የመረጠላቸውን ባል አለማግባት
  • ወሲባዊ ጥቃት ወይም መደፈር ሲፈፀምባቸው
  • ከጋብቻ ውጭ ወሲባዊ ግንኙነት ቢኖራቸው ወይም ኖሯቸዋል ተብሎ የሚታመን ከሆነ

ከዚህም በተጨማሪ አለባበሳቸው 'ያልተገባ' ከሆነ፣ 'የማይሆን' ጠባይ ካሳዩ እንዲሁም 'ታዛዥ' ካልሆኑ ግድያው ይፈፀምባቸዋል ተብሏል።