የትዋይላይት ፊልም ተዋናይ ግሪጎሪ ታይሪና የሴት ጓደኛው ሞተው ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በታዋቂው 'ትዋይላት' ፊልም ላይ የተወነው ግሪጎሪ ታይሪ ቦይስና የሴት ጓደኛው ላስ ቬጋስ ውስጥ ሞተው ተገኙ።
ተዋናዩ በጎርጎሳውያኑ 2008 በተሰራው በመጀመሪያው ክፍል ትዋይላይት ላይ በመተወን ዝናን አትርፎ ነበር።
ግሪጎሪ 30 ዓመቱ ሲሆን የሴት ጓደኛው ናታሊ አዴፖጁ ደግሞ 27 ዓመቷ ነው።
ፖሊስ ምንም እንኳን ምርመራውን ባያጠናቅቅም ያሉትን ሁኔታዎች በመገምገም ወንጀል እንዳልተፈፀመባቸው አስታውቋል።
ግሪጎሪ ቦይስ በቫምፓየር (የሰውን ደም እየመጠጡ በሚኖሩ) ህይወት ላይ በሚያጠነጥነው የትዋይላይት ፊልም ላይ ታይለር የሚባልን ገፀ ባሕሪይ ወክሎ ተጫውቷል። በአንደኛው በማይረሳ ትዕይንት ላይ መኪናውን እያበረረ ቤላ የምትባለውን ገፀ ባሕሪይ ሊገጫት ሲል ዋነኛው ተዋናይ ኤድዋርድ የተባለው ቫምፓየር በባዶ እጁ መኪናውን ሲያቆመው ያሳያል።
ሞቱ ከተሰማ በኋላ በርካቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሃዘናቸውን የገለፁ ሲሆን ወንድሙ ክሪስ ዌይንም "ወንድሜ አብረኸኝ ብትሆን እንዴት ደስ ይለኝ ነበር። ዓለም ድንቅ የሚባል ሰው አጣች" በማለት ልቡ መሰበሩን በፌስ ቡክ ገፁ ላይ አስፍሯል።
እናቱም ሊዛ ዌይን "ያላንተ ህመም ላይ ነኝ። ተበጣጥሻለሁ፤ ሁሉ ነገር ጠፍቶብኛል። ከፍተኛ የልብ ስብራት ላይ ነኝ" በማለት ሃዘኗን የገለፀች ሲሆን አክላም "በሆነ ምክንያት ሲጨንቀኝም ሆነ ስረበሽ መልዕክት እልክልሃለሁ ወይም እደውልሃለሁ። አንተም በምላሹ 'እማ ሁሌም ከጎንሽ ነኝ፤ ችግሩን አብረን እንጋፈጠዋለን' ትለኛለህ። ልጄ ለምን ትተኸኝ ሄድክ?" ብላለች።
"ከዚህ በኋላ መቼም ቢሆን እቅፍ አድርህ አትስመኝም። እነዚህንም ቃላቶች ደግሜም አልሰማቸውም። ልጄ እወድሃለሁ። ስብርብር ብያለሁ። በጣም እወድሃለሁ ግሬጊ፤ የኔ ማር" በማለት እናቱ አንጀት የሚበላ ሃዘኗን ገልጻለች።
ግሪጎሪና ናታሊ የዶሮ ጥብስ የሚሸጥበት ትልቅ ሬስቶራንት የመክፈት እቅድ እንደነበራቸውና፤ ለማጠናቀቅም ጥቂት እንደቀራቸው እናቱ ተናግራለች።
"በአጭሩ የተቀጨው"
ግሪጎሪ የአስር ዓመት ሴት ልጅ ያለችው ሲሆን፤ የሴት ጓደኛው ናታሊ ደግሞ ህፃን ወንድ ልጅ አላት።
የናታሊን ቀብር የሚያስፈፅሙት በበኩላቸው በሰጡት መግለጫ "ናታሊ ብዙ ዕቅድ የነበራትና ህይወትንም ገና እየጀመረች ነበር። እንዲህ በአጭሩ ህይወቷ በመቀጨቷ አዝነናል" ብለዋል።
የላስ ቬጋስ ባለስልጣናት ዩኤስ ኤ ቱዴይን ጨምሮ ለተለያዩ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ የአሟሟታቸው ምክንያትን በተመለከተ ገና የላብራቶሪ ውጤት እየተጠበቀ ነው በማለት አስረድተዋል።
የፖሊስ ቃለ አቀባይ ላሪ ሃድፊልድ ለላስ ቬጋስ ሪቪው ጆርናል እንደተናገሩት "አሟሟታቸው ወንጀልን አያመላክትም" ብለዋል።












