ሱዳን በምስራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ጥቃት ለተጎዱ ካሳ መክፈል አለባት ተባለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሱዳን በጎርጎሮሳዊያኑ 1998 ኬንያና ታንዛኒያ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ አልቃይዳ በፈጸመው የቦምብ ጥቃት ለተጎዱ ካሳ እንዲትከፍል የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ አሳለፈ።
በጥቃቱ ከ200 በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን በሺህዎች የሚቆጠሩ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ሱዳን ለአልቃይዳ እና ለቡድኑ መሪ ኦሳማ ቢንላደን ቴክኒካዊ እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች በሚል ነበር የተከሰሰችው።
ውሳኔው የተላለፈውም አዲሱ የሱዳን መንግሥት አሜሪካ ሽብርተኛን ይደግፋሉ ካለቻቸው አገራት ዝርዝር ውስጥ አገራቸው እንድትሰረዝ ግፊት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።
ሱዳንን የወከሉት ክርስቶፈር ኩራን፤ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተላለፈው ውሳኔ በጎርጎሮሳዊያኑ 2011 የተላለፈውንና ከ4 ቢሊየን ዶላር በላይ ቅጣት ውስጥ 800 ሚሊየን ዶላር ለጉዳት ካሳ ያቀረበችው ገንዘብ እንደገና ተነስቷል ማለታቸውን ጠቅሶ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ከ9 ዓመታትም በፊት በዋሽንግተን የፌደራል ፍርድ ቤት ሱዳን 6 ቢሊየን ዶላር ካሳ እንዲሁም 4 ቢሊየን ዶላር የጉዳት ቅጣት እንድትከፍል ማዘዙን ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
በጎርጎሮሳዊያኑ 2017 ደግሞ ሱዳን የቅጣት ውሳኔውን ተከትሎ ክሱ የተመሰረተው በ2008 በተሻሻለው ሕግ ሲሆን ይህም ከ20 ዓመታት በፊት ለሆነ ነገር አይሰራም ስትል ስትከራከር ቆይታለች።
ይሁን እንጂ ጠቅላይ ፍድ ቤቱ ኮንግረንሱ ሕጉን ወደኋላ ተመልሶ መጠቀም ይችላል በማለቱ ሰኞ ዕለት ውሳኔውን አስተላልፏል።
እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ሱዳን በሽብር ጥቃቱ ለተጎዱት የተሰማትን ሃዘን ትገልጻለች፤ ነገር ግን በእንደዚህ ዓይነት የተሳሳተ ተግባር ላይ ተሳታፊ እንዳልነበረችና ምንም ግንኙነት እንደሌላት ኩራን ተናግረዋል።
አዲሱ የሱዳን መንግሥት ባለፈው ዓመት ለረዥም ዓመታት ሱዳንን ያስተዳደሩት ኦማር አል በሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ አገሪቷ ከኢኮኖሚ መገለሉን ለማቆም የሚረዳትንና ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማደስ እየሞከረች ነው።
ኦማር አል በሽር በሙስና ወንጀል ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ እስር ቤት የሚገኙ ሲሆን በአሜሪካ መርከብና እና ኤምባሲዎች ላይ ጥቃት ሲፈጸም በሥልጣን ላይ ነበሩ።












