ኮሮናቫይረስ ፡ በፓኪስታን በኦክስጅን እጥረት ሳቢያ ህሙማን ሞቱ

በፓኪስታን የኦክስጅን እጥረት የኮቪድ-19 ህሙማንን ገደለ

የፎቶው ባለመብት, EPA

በፓኪስታን የኦክስጅን እጥረት ገጥሞ ስድስት የኮቪድ-19 ህሙማን ሕይወታቸው አለፈ።

ፐርሽዋር በምትባል ግዛት የሚገኝ የመንግሥት ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና ላይ የነበሩ ህሙማን ናቸው የሞቱት።

የህሙማኑ ቤተሰቦች ነፍሳቸውን ለማዳን ሲማጸኑ እንደነበረም ተነግሯል።

ኦክስጅን በመዘግየቱ ሳቢያ 200 ህሙማን የኦክስጅን መጠን ተቀንሶባቸዋል።

የሆስፒታሉ አመራሮች ኦክስጅን አቅራቢውን ወቅሰዋል። ብዙ ሠራተኞችም ተባረዋል።

ፓኪስታን ውስጥ ወረርሽኙ እንደ አዲስ አገርሽቷል። 400,000 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው 8,000 ሞተዋል።

ካይበር ቲቺንግ በተባለው ሆስፒታል ቅዳሜ የሚጠበቀው ኦክስጅን ሳይደርስ በመቅረቱ ህሙማኑ ለሞት ተዳርገዋል።

300 መጠባበቂያ ሲሊንደሮች ቢኖሩም ቬንትሌተሮችን የማንቀሳቀስ ጉልበት አልነበራቸውም ተብሏል።

እናቱ በኮሮናቫይረስ የተያዘችው ሙራድ አሊ ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ ሆስፒታሉ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን ለማዳን ሲሯሯጡ ነበር።

“ሀኪሞቹን ስንለምናቸው ነበር። አንዳንድ ህሙማን ወደ ድንገተኛ ክፍል ተዘዋወሩ” ብሏል።

ድንገተኛ ክፍል ውስጥ የነበረው ኦክስጅን ሲገባደድ ግን ሰዎች እንደሞቱና ብዙዎች ህመማቸው እንደተባባሰባቸው ተናግሯል።

የሆስፒታሉ ሠራተኞች የህሙማን ቤተሰቦች ኦክስጅን እንዲገዙ ቢጠይቁም ሁሉም የመግዛት አቅም እንዳልነበራቸው ሙራድ ገልጿል።

የሆስፒታሉ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ከሞቱት ህሙማን አምስቱ ኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ናቸው። አንዱ ታማሚ ደግሞ በጽኑ ህሙማን ማቆያ ሲታከም ነበር።

የሆስፒታሉ አመራሮች ኦክስጅን መዘግየቱ “በወንጀል የሚያስጠይቅ ቸልታ ነው” ብለዋል።

ኦክስጅኑን ለሆስፒታሉ እንዲያደርስ የተመደበ ባለሙያ በቦታው እንዳልነበረ በምርመራ ተድርሶበታል።

የሆስፒታሉን ዳይሬክተር ጨምሮ ሌሎችም ብዙ የሆስፒታሉ ሠራተኞች ከሥራ ታግደዋል።