አፍጋኒስታን ውስጥ በሆስፒታል ላይ በተፈጸመ ጥቃት ህጻናትና እናቶች ተገደሉ

አንድ ወታደር ህጻን ልጅ ይዞ

የፎቶው ባለመብት, AFP

አፍጋኒስታን ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሁለት ህጻናት እንዲሁም 11 እናቶችና ነርሶች ተገደሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ህጻናትን ጨምሮ 15 ሰዎች ዛሬ ማክሰኞ በርካታ ታጣቂዎች ካቡል ውስጥ የሚገኘውን ሆስፒታል ባጠቁበት ወቅት መቁሰላቸውን ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ኤምኤስኤፍ የሚባለው ድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን የሆስፒታሉእን አንድ ክፍል የሚያስተዳድረው በመሆኑ የተወሰኑ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች በሆስፒታሉ ውስጥ ይሰራሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በምሥራቃዊ አፍጋኒስታን በአንድ የፖሊስ አባል የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 21 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ በቦንብ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በሁለቱም ጥቃቶች የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል ተሰግቷል።

አንድ ጥቃቱ ከተፈጸመበት ሆስፒታል ሸሽቶ የወጣ ዶክተር ለቢቢሲ እንደተናገረው ጥቃቱ ጠዋት አራት ሰዓት ላይ ሲፈጸም 180 ያህል ሰዎች በሆስፒታሉ ውስጥ ነበሩ።

ጥቃቱ የተፈጸመበት ሆስፒታል

የፎቶው ባለመብት, AFP

በጥቃቱ ወቅት የአፍጋኒስታን ልዩ ኃይሎች ሦስት የውጪ አገር ዜጎችን ጨምሮ 100 የሚሆኑ ሴቶችና ህጻናትን ከሆስፒታሉ ማስወጣታቸውን አንድ ባለስልጣን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች ወደ ሆስፒታሉ የፖሊስ ልብስ ለብሰው የገቡ ሲሆን ለሰዓታት በቆየ የተኩስ ልውውጥ የጥበቃ ሠራተኞችን መግደላቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ናንጋርሃር በተባለችው የአፍጋን ምሥራቃዊ ግዛት ዛሬ በተመሳሳይ በአንድ የፖሊስ አዛዥ ቀብር ላይ በተፈጸመው ጥቃት የግዛቲቱ ምክር ቤት አባልን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ሲገደሉ 55 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

በጥቃቱ የተጠረጠረው ታሊባን ስለድርጊቱ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ በመግለጹ ጥቃቱን የፈጸመው ቡድን ማን እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። ከዚህ በፊትም ስለተፈጸሙ ጥቃቶች ቡድኑ በተመሳሳይ እጁ እንደሌለበት አሳውቋል።

ሪፖርቶች እንዳመለከቱት በሰሜናዊ አፍጋኒስታን ሃልካህ ግዛት የአሜሪካ ኃይሎች በፈጸሙት የአየር ጥቃት ቢያንስ 10 ሰዎች ሲገደሉ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸው ተነግሯል።

የአካባቢው ነዋሪዎች የጥቃቱ ሰለባዎች ሰላማዊ ሰዎች እንደሆኑ ቢገልጹም የአፍጋን መከላከያ ሚኒስቴር ግን በአየር ጥቃቱ የተገደሉት ሸማቂዎች ናቸው ብለወል።

ታሊባን በየካቲት ወር ላይ ከአሜሪካ ጋር እያደረገው የነበረው ድርድር የእስረኞች ልውውጥን በተመለከተ ከስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ግጭቱ መቋጫ ሳያገኝ ቀርቷል። በዚህ ድርድር ላይ አይኤስ ተሳታፊ አልነበረም።