ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይጠበቅ አፍጋኒስታን ሄዱ

ፕሬዝደንት ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አፍጋኒስታን የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮችን ጎበኙ።

ትራምፕ ጉብኝት እንደሚያካሂዱ ሳያሳውቁ፤ 'ቴንክስጊቪንግ' የተባለውን በዓል አስታከው ወደ አፍጋኒስታን በማቅናት ከወታደሮች ጋር ተገናኝተዋል።

በ 'ባግሪም ኤርፊልድ' የተገኙት ፕሬዘዳንቱ፤ አሜሪካ ከታሊባን ጋር እየተወያየች መሆኑን፣ ታሊባኖች "ስምምነት እንደሚፈልጉም" ለወታደሮቹ ተናገረዋል።

ትራምፕ ወደ አፍጋኒስታን ሲሄዱ ይህ የመጀመሪያቸው ሲሆን፤ ከአፍጋኒስታን ፕሬዘዳንት አሽራፍ ጋኒ ጋርም ተገናኛተዋል።

ከታሊባን ጋር ወደ ሰላማዊ ስምምነት ለመመለስ ሲባል፤ የእስረኞች ልውውጥ መካሄዱን ተከትሎ ነው ትራምፕ ወደ አፍጋኒስታን የሄዱት። አሜሪካ ወታደሮቿን "በእጅጉ እየቀነሰች ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።

አሜሪካ እአአ የደረሰውን የመስከረም 11 ጥቃት ተከትሎ፤ በአፍጋኒስታን ጣልቃ ከገባች 18 ዓመት የሞላ ሲሆን፤ አሁን በአፍጋኒስታን 13,000 ወታደሮች ይቀሯታል።

ትራምፕ ጉብኝታቸውን ያካሄዱት፤ ታሊባን ለአራት ዓመታት ታግተው የነበሩ ሁለት ምዕራባውያን ምሁራንን ነፃ ከለቀቁ በኋላ ነው። በምላሹም ሦስት ታጣቂዎች ነፃ ተደርገዋል።

"ከታሊባን ጋር ስንነጋገር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ ፈልገን ነበር። እነሱ ግን አልፈለጉም፤ አሁን ግን የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ ፈልገዋል" ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።

ውይይቱ ምን ያህል መስመር እንደያዘ የታወቀ ነገር የለም።

የአፍጋን ባለሥልጣኖች ለረዥም ጊዜ ከታሊባን ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ሲሞክሩ እንደነበር ይታወሳል። እአአ በ2001 ታሊባንን ማስወጣት ከተቻለበት ጊዜ አንስቶ ከነበረው የታሊባን ይዞታ የአሁኑ ይሰፋል። ታሊባን ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ከአፍጋን ባለሥልጣኖች ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ አይደለም።

የታሊባን መሪዎች፤ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ፣ ዶሃ ውስጥ ከአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ቢያረጋግጡም፤ ሮይተርስ እንደዘገበው ግን መደበኛ ውይይቱ አልቀጠለም።

ትራምፕ የወታደሮችን ቁጥር ወደ 8,600 ለመቀነስ እቅድ እንዳላቸው ቢናገሩም፤ ወታደሮች መቼ እንደሚወጡ ያሉት ነገር የለም። "ስምምነት ላይ እስክንደርስ ወይም ሙሉ በሙሉ እስክናሸንፍ ድረስ እንቆያለን፤ ስምምነት ላይ መድረሱን ደግሞ አጥብቀው ይፈልጉታል" ሲሉ ተናግረዋል።