ታሊባን፡ የሰላም ድርድሩ መቋረጥ የሚጎዳው አሜሪካንን ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የታሊባን ከፍተኛ መሪዎች የሰላም ድርድሩ መቋረጡ በዋነኛነት የሚጎዳው አሜሪካንን እንጂ እኛ አይደለም አሉ።
ታሊባን ባወጣው የጽሁፍ መግለጫ በሁለቱ አካላት መካከል ሲደረግ የነበረው የሰላም ድርድር እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነበር ብሏል።
ይህ የሰላም ድርድር በአፍጋኒስታን ለ18 ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም እድል ይሰጥ ነበር በማለት የታሊባን መሪዎች ለድርድሩ መቋረጥ አሜሪካንን ተጠያቂ አድርገዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከታሊባን ጋር እየተካሄደ የነበረውን የሰላም ስምምነት ስለመሰረዛቸው ትናንት ማስታወቃቸው ይታወሳል።
ሐሙስ ዕለት በአፍጋኒስታን መዲና ካቡል በተፈጸመው እና ታሊባን ኃላፊነቱን በወሰደው ጥቃት አንድ የአሜሪካ ወታደር መገደሉን ትራምፕ የሰላም ስምምነቱን ለመሰረዝ ምክንያት ሆኗቸዋል።
አሜሪካዊው ወታደር መገደሉ ከተሰማ በኋላ፤ ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ "በአስቸኳይ ውይይቶቹ እና የሰላም ድርድሩ እንዲቆም አዝዣለሁ" ብለዋል።
በጥቃቱ ከአሜሪካዊው ወታደር በተጨማሪ ሌሎች 11 ሰዎች ተገድለዋል።
ሁለቱ አካላት ከሰላም ስምምነት እንዲደርሱ የአሜሪካ መንግሥት እና የታሊባን ተወካዮች በኳታር ዶሃ ከዘጠኝ ጊዜ በላይ ተገናኝተው መክረዋል። የሰላም ስምምነቱ አደራዳሪዎች ከቀናት በፊት አሜሪካ እና ታሊባን 'በመርህ ደረጃ' ከሰላም ስምምነት ደርሰዋል ብለው ነበር።
የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢሁላህ ሙጀሂድ በካቡል በሰጡት መግለጫ የደረሰውን ጥቃት ምክንያት በማድረግ የሰላም ድርድሩን ማቋረጣቸው አሜሪካዊያኑ ብስለት እና ልምድ እንደሚጎድላቸው ያሳያል ብለዋል።
ቃለ አቀባዩ እንደሚሉት ከሆነ ታሊባን እና የአፍጋኒስታን መንግሥት ከ12 ቀናት በኋላ ተገናኘተው ሊመክሩ ቀጠሮ ይዘዋል።
የሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚ ቢሆን ኖሮ አሜሪካ ወደ አፍጋኒስታን ካዘመተቻቸው ወታደሮች መካከል 5400 የሚሆኑት በ20 ሳምንታት ውስጥ ልታስወጣ ነበር።
እ.አ.አ. 2001 መስከረም 1 ላይ በአሜሪካ ላይ ከተሰነዘረው ጥቃት በኋላ ነበር አሜሪካ ለአሸባሪ ቡድኖች ድጋፍ ያደርጋል ያለችውን የታሊባን መንግሥትን ከስልጣን ለማውረድ አፍጋኒስታንን የወረረችው።
በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ በአፍጋኒስታን ከ14ሺህ በላይ ወታደሮች አሏት።
ታሊባን በምፈጽማቸው ጥቃቶች ዒላማ የማደርው የውጪ ሃገር ኃይሎችን ነው ይበል እንጂ በጥቃቶቹ ለከፍተኛ ጉዳት የሚዳረጉት ንጹሐን የአፍጋኒስታን ዜጎች ናቸው።
አሜሪካ አፍጋኒስታንን ከወረረች ወዲህ ከ3500 በላይ የውጪ ሃገራት ጥምር ኃይሎች ተገድለዋል። ከእነዚህም መካከል 2300 የሚሆኑት አሜሪካውያን ናቸው።
ባለፉት 18 ዓመታት ምን ያክል የአፍጋኒስታን ሲቪሎች፣ የመንግሥት ወታደሮች እና ታጣቂ ሚሊሻዎች ህይወታቸውን እንዳጡ በውል አይታወቅም።
ከወራት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው ሪፖርት ከ32ሺህ በላይ ሲቪሎች ተገድሏል ያለ ሲሆን ሌሎች ተቋማት በበኩላቸው የውጪ ኃይሎችን ሲፋለሙ የነበሩ ከ42 ሺህ በላይ ሚሊሻዎች መገደላቸውን ይጠቁማሉ።












