ኮሮናቫይረስ፡ ዋይት ሀውስ በዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ ንግግር ተቆጣ

ፋውቺና ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS

ዋይት ሀውስ፤ ከፍተኛ የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ፤ ስለ ኮሮናቫይረስ ያደረጉት ንግግር ፖለቲካዊ አላማ ያለው ነው ሲል ከሰሰ።

ዶ/ር ፋውቺ ከዋሽንግተን ፖስት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ አሜሪካ “ከፍተኛ ጉዳት ገጥሟታል” ብለዋል።

አሜሪካ ከየትኛው አገር በበለጠ በወረርሽኙ ሳቢያ ዜጎቿን አጥታለች።

በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ መሠረት ከ230,000 በላይ ሰዎች ሞተዋል። ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ደግሞ በቫይረሱ ተይዟል።

ዶ/ር ፋውቺ በቃለ ምልልሱ ላይ “ወደቀዝቃዛው ወቅት ስንገባ ነገሮች ይባባሳሉ” ብለዋል።

በተያያዥም ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን ስለ ወረርሽኙ ያላቸውን አቋም ገምግመዋል።

ባይደን ለቫይረሱ ተገቢውን ትኩረት እንደሰጡት “ከሕብረተሰብ ጤና እና ከምጣኔ ሀብት አንጻርም በቁምነገር እየተከታተሉት ነው” በማለት ገልጸዋል።

አሜሪካ የሕብረተሰብ ጤናን በተመለከተ ለውጥ ማምጣት እንዳለባት አሳስበዋል።

በዚህ የዶ/ር ፋውቺ አስተያየት ዋይት ሀውስ ደስተኛ አልሆነም። ባይደን ምርጫውን እንዲያሸንፉ የሚገፋ ምላሽ ነው በማለትም ዶክተሩን ተችተዋል።

ቃል አቀባዩ ጁድ ደሬ፤ “አስተያየቱ ተቀባይነት የለውም። ከመርህ ውጪ ነው። ዶ/ር ፋውቺ የኮሮናቫይረስ ግብረ ኃይል አባል እንደመሆናቸው ለለውጥ መገፋፋት ነበር የሚጠበቅባቸው። እሳቸው ግን ፕሬዘዳንቱን በመተቸት ለተቀናቃኛቸው ወገንተኝነት አሳይተዋል” ብሏል።

የወረርሽኙ ጉዳይ በትራምፕ እና በባይደን መካከል ዋነኛ ከሆኑት መከራከሪያ ነጥቦች አንዱ ነው።ባይደን “ውሳኔያችን ሳይንስን የተመረኮዘ መሆን አለበት” ብለው፤ ምርጫውን ካሸነፉ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው፤ ባይደን እንቅስቃሴ ላይ ገደብ በመጣል አሜሪካውያንን የምጣኔ ሀብት ቀውስ ውስጥ ይከታሉ ብለዋል።

“ባይደንን ከመራጥችሁ ትምህርት ቤት አይከፈትም። ተማሪዎች አይመረቁም። ሠርግ አይኖርም። ገና አይከበርም” ብለዋል።

ባይደን የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የወጡ መርሆችን ተከትለው ነው። በሌላ በኩል ትራምፕ አካላዊ ርቀት ሳይጠበቅ በርካታ ዜጎች የተገኙባቸው የምረጡኝ ቅስቀሳዎች አካሂደዋል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ኮሮናቫይረስ በፕሬዝዳንት ትራምፕ አንደበት!
ኮሮና
Banner