በቱርክ እና በግሪክ የደረሰው ርዕደ መሬት የሰዎችን ህይወት ቀጠፈ

የኢዝሚር ግዛት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በቱርክ የኤጂያን ጠረፍ እና በሰሜናዊ የግሪክ ደሴት ሳሞስ በደረሰ ከባድ ርዕደ መሬት ቤቶችን ሲያወድም ቢያንስ 22 ሰዎች ሞተዋል፡፡

እንደአሜሪካ ስነ ምድር ጥናት ከሆነ ርዕደ መሬቱ በቱርክን ኢዝሚር ግዛትን ሲከሰት በሬክተር ስኬል 7.0 ተመዝግቧል፡፡

ቱርክ በበኩሏ ቁጥሩን ወደ 6.6 ዝቅ ስታደርግ በኢዝሚር ግዛት 20 ሰዎች ሲሞቱ እንዲሁም 786 ሰዎች ቆስለዋል ብላለች፡፡ በሳሞስ ደግሞ የሁለት ታዳጊዎች ህይወት አልፏል፡፡

ጥልቀት ባለው ቦታ የተከሰተው መንቀጥቀጥ ኢዝሚርን እና ሳሞስን በጎርፍ ያጥለቀለቀ አነስተኛ ሱናሚ አስነስቷል ፡፡

ተጨማሪ ሕንፃዎች ሊፈርሱ ይችላሉ በሚል ስጋት የኢዝሚር ባለሥልጣናት 2 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን የሚይዙ የድንኳን እያዘጋጁ ነው፡፡

እንደባለስልጣናቱ ከሆነ 70 ሰዎችን ከፍርስራሽ ስር ታድገዋል ፡፡

ተጨማሪ ሰዎችን ለማትረፍ ፍርስራሽ ሥር የሚደረገው ፍለጋ ቀጥሏል ተብሏል፡፡

እንደአሜሪካ ስነ ምድር ጥናት ከሆነ ርዕደ መሬቱ 10 ኪሜ ጥልቀት ላይ የተፈጠረ እና ንዝረቱ በመዲናዎቹ አቴንስ እና ኢስታንቡል ድረስ ተሰምቷል። የቱርኩ ባለሥልጣናት ግን ከመሬት በታች 16 ኪ.ሜ ነው የተከሰተው ብለዋል።

ቱርክ እና ግሪክ ለርዕደ መሬት አዲስ አይደሉም፡፡

ወደ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ያላት የቱርኳ ሦስተኛ ከተማ ኢዝሚር ርዕደ መሬት ከተከሰተ በኋላ ብዙ ሰዎች በፍርሃት ወደ ጎዳና ሲሮጡ ታይተዋል፡፡ አደጋውን ተከትሎ ቢያንስ 20 ሕንፃዎች ወድመዋል ፡፡

አንድ ህንፃ የወደቀበትን ቅጽበት የሚያሳይ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያዎች ተሰራጭቷል፡፡ በሌሎች ቪዲዮዎች ደግሞ ሰዎች ፍርስራሽ ስር ሰዎችን ሲፈልጉ ታይተዋል፡፡

የባህር ከፍታ መጨመሩን ተከትሎ የጎርፍ መጥለቅለቅ እንደደረሰ መረጃዎች ሲጠቁሙ አንዳንድ አሳ አጥማጆችም የደረሱበት አልታወቀም ተብሏል ፡፡

"ከእግር ሊነቀንቅ የሚችል በጣም ጠንካራ መንቀጥቀጥ ነበር፡፡ ከልጆቼ ጋርወደ ውጭ ስንሮጥ የሰከርን ነበር" ብክሪስ ቤድፎርደ የተባሉ ጡረተኛ መምህር ከምዕራብ ኢዝሚር ገልጸዋል፡፡ .

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ታይብ ኤርዶጋን መንግሥት በርዕደ መሬት የተጎዱትን "ባለው አቅም ሁሉ" እንደሚረዳ ተናግረዋል ፡፡

በግሪክ ሳሞስ ግድግዳ ፈርሶ ሁለት ታዳጊዎች ሞተዋል፡፡ በደሴቲቱ ደግሞ ስምንት ሰዎች ቆስለዋል፡፡

አነስተኛ ሱናሚ የሳሞስን ወደብ በጎርፍ አጥለቅልቆት በርካታ ሕንፃዎች ተጎድተዋል፡፡ የግሪክ ባለሥልጣናት ርዕደ መሬቱን መጠን 6.7 ሬክተር ስኬል ነው ብለዋል፡፡

"ርእደ መሬቱ በጣም ነው የተሰማን" ያለው ጋዜጠኛ ማኖስ ስታናኪስ ሲሆን አነስተኛ ንዝረቶችም መቀጠላቸውን አክሎ አስረድቷል፡፡

ከ1904 ወዲህ በደሴቲቱ ላይ የደረሰው ከፍተኛ መንቀጥቀጥ ነው ብሏል ፡፡

ነዋሪዎቹ ከቤት ውጭ እንዲቆዩ እና ከባህር ዳርቻ አካባቢዎች እንዲርቁ ጥሪ ቀርቧል፡፡ በሳሞስ 45 ሺህ ያህል ሰዎች ይኖራሉ ፡፡