በኢትዮጵያ ያሉ ኤርትራውያን ስደተኞች መድልዎ እየደረሰባቸው እንደሆነ ገለፁ

በኢትዮጵያ ያሉ ኤርትራውያን ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, IOM

በመቶ ሺዎች የሚሆኑ ስደተኞችን በመጠለያ ማዕከላት በምትቀበለው ኢትዮጵያ ወደ አገሪቷ የሚገቡ ኤርትራውያን ስደተኞች መድልዎ እየደረሰባቸው እንደሆነ ቅሬታቸውን አሰሙ።

ኤርትራውያን ስደተኞቹ "ወታደሮችና የመንግሥት ሰራተኞች" ያልሆናችሁ ወደ ስደተኞች ካምፕ አትገቡም በሚል ተከልክለናልም እያሉ ነው።

ከኤርትራ በተለያዩ ምክንያቶች ጠፍተው የመጡና የኢትዮጵያ ድንበርንም አቋርጠው የገቡ ስደተኞች በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል በሚገኙ የድንበር ከተሞች ተጠልለውም ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ይናገራሉ።

በዓዲግራት፣ ዛላምበሳ፣ ሽራሮ፣ ዓዲ ነብር፣ ራማ እና ገርሁስርናይ በሚባሉት ከተሞችም ስደተኞቹ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተጠልለው እንዳሉም ቢቢሲ ለመረዳት ችሏል።

ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር መሰረት ወደ ኢትዮጵያ ተሻግረው የሚገቡ ኤርትራውያን ስደተኞች በድንበር አካባቢ በሚገኙ ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ እንዲቆዩ ይደረግ ነበር።

ከባለፈው አመት ጥር ወር ጀምሮ እነዚህ ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከላት የተዘጉ ሲሆን የስደተኞችና ከስደት ተመላሽ ጉዳዮች ኤጀንሲ ሰራተኞች ኤርትራውያን ወደሚገኙበት የለይቶ ማቆያ ቦታ በመሄድም የምዝገባና የማጣራት ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ።

በዓዲግራት ዩኒቨርስቲ የለይቶ ማቆያ ጊዜያቸውን ጨርሰው በአሁኑ ወቅት በቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ኤርትራውያን ስላሉበት ፈታኝ ሁኔታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለደህንነቴ ሲባል ስሜ አይጠቀስ ያለችው የ22 ዓመቷ ኤርትራዊ ከ18 አመት በላይ የሆናቸው ኤርትራውያን የብሄራዊ አገልግሎት አካል የሆነው የሳዋ ማሰልጠኛ ማእከል መግባታቸው አስገዳጅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም እሷ ስለማታምንበት ሸሽታ መሰደዷን ትናገራለች።

ከኢትዮጵያ የስደተኞች ካምፕ የሚመጡ ባለሞያዎች ወታደሮች ለይተው እየወሰዱ እንደሆነ ተናግራለች::

"ዓለምአቀፍ የስደተኞች ጉዳይ የሚመለከተው ተቋም ሁሉንም ስደተኞች በእኩል እንደሚያይ ነበር የምናውቀው። እዚህ ከመጣን በኋላ ግን መድልዎ እንደሚፈፀም እየተመለክትን ነው:: ወታደሮችን ለይተው ሲወስዱ አይተናል:: እኛም ውትድርናን ሸሽተን ነው የመጣነው" በማለትም ትናገራለች።

እስካሁንም ባለው ወቅት የዓዲግራት ህዝብ ቁርስ፣ ምሳና እራት እያቀረበ የመገባቸው ቢሆንም በባለፉት ሁለት ቀናት ግን በመቋረጡ መቸገራቸውን ትገልፃለች።

ከዚህም በተጨማሪ "በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ" በአሁኑ ወቅት ስደተኞቹ የተጠለሉበት ኮሌጅ ትምህርት ለመጀመር ፅዳት እያካሄዱም በመሆኑ መውደቂያቸው እንዳሳሰባቸው ጭንቀትዋን አጋርታለች።

"ወደየትም እንደምንሄድ አስጨንቆናል" ብላለች።

በተመሳሳይ ለደህንነቷ ስሜ ይደበቅ ያለችና ከደቡባዊ ዞን ሰንዓፈ ከተማ የመጣችው የ19 ዓመቷ የ11ኛክፍል ተማሪ በበኩሏ መጠለያ የሚጠይቅ ስደተኛ እንዴት መብቱ እንደሚታገድ ግራ እንደተጋባች ትናገራለች።

ከኤርትራ ከመጣችበት እለት ጀምሮ አንድ ወር ከሁለት ሳምንት በለይቶ ማቆያ ውስጥ መቆየቷ በጣም እንዳሳዘናት ገልፃ ለምን ወደ ስደተኞች ካምፕ እንደማያስገቧቸውም በምትጠይቅበትም ወቅት ግልፅ መልስ የሚሰጣቸውም አካል እንዳላገኙ ትናገራለች።

ዓዲግራት ከተማ በሚገኘው የቴክኒክና የሙያ ማሰልጠኛ ማዕከልም ከነበሩት 130 ኤርትራውያንም መካከል 30 የሚሆኑት ብቻ ወደ ስደተኞች ካምፕ መወሰዳቸውንም ለቢቢሲ ገልፃለች።

"በቋንቋ መግባባት የማይችሉ ህፃናት የያዙ እናቶች ደም እያነቡ ይገኛሉ" በማለት ችግሩ ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ታስረዳለች።

በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል በሚገኙ አራት የስደተኞች መጠለያ ካምፕ እንዲሁም በአፋር ክልል በሚገኘው አንድ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ በሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያንም ሰፍረው ይገኛሉ።

ከአንድ ዓመት በፊት በነበረው አሰራር ወደ ስደተኞች ካምፕ ለመግባት መስፈርትም ሆነ ምንም ዓይነት ክልከላ እንዳልነበር ይታወቃል።

በቅርቡ ግን ወደ ስደተኞች ካምፕ ለማግባት የማጣራት ስራው እየከረረና እየጠበቀ የመጣ መሆኑንም በመግለፅ ወታደሮችና የመንግሥት ሰራተኞች ያልሆኑትን ስደተኞች ወደ ካምፑ እንዳይገቡ መከልከላቸው አግላይ መሆኑንም ይናገራሉ።

በአሁኑ ወቅት በዓዲግራት 105፣ በራማ 95፣ በዛላምበሳ 44፣ በገርሁስርናይ 124፣ በዓዲ ነብርእድ 53፣ እንዲሁም በሸራሮ 460 በአጠቃላይ 881 ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ካምፕ ለመግባት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ቢቢሲ ከተለያዩ ምንጮች ባጠናቀረው መረጃ መረዳት ችሏል።

"ወደ ስደተኞች ካምፕ እንዳንገባ ተከልክለናል" የሚለውን ቅሬታም በሚመለከት ቢቢሲ ጥያቄ ያቀረበላቸው የስደተኞችና ከስደት ተመላሽ ጉዳዮች ኤጀንሲ ሰራተኛ ከዚህ ቀደም የነበረው የስደተኞች አቀባባበል አሰራር ተሻሽሏል ብለዋል።

ስሜ አይገለፅ ያሉት እኚሁ ሰራተኛ ኤርትራዊ መሆን ብቻ ወደ ስደተኞች ካምፕ ለመግባት እንደ ቅድመ ሁኔታ እንደማይቀርብና በተሻሻለው አዋጅ መሰረት መመዘኛውን የሚያሟሉ ብቻ ተጣርተው እንደሚገቡ አስታውቀዋል።

በተለይም ደግሞ ከኤርትራ ተነስተው በአውሮፕላን በአዲስ አበባ በኩል የሚመጡትን ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ካምፕ መግባት እንደማይችሉም ገልፀዋል።