ስደት፡ የኤርትራውያን ዋይታ የተሰማባት ላምፔዱሳ

የፎቶው ባለመብት, YOSEPH AND ADHANOM
መስከረም 23 ኤርትራውያኖቹ ዮሴፍና አድሓኖም በጣልያኖቹ ሲሲሊ፣ ላምፔዱሳ፣ ፓልርሞና ካታንያ ከተሞች ላይ የሚገኙ ህዝባዊ የመቃብር ቦታዎችን በየአመቱ ይጎበኛሉ።
መቃብሮቹ ስም የላቸውም፣ ማንነታቸውም አይታወቅም፤ አንዱን ከአንዱ ለመለየትም በኮድ ቁጥር ተቀምጦላቸዋል። ዮሴፍና አድሓኖም ፎቶ ያነሳሉ፤ ቪዲዮ ይቀርፃሉ፤ ጥልቅ ሃዘናቸውንም ይገልፃሉ።
በየአመቱ ይህችን ቀን መቼም ቢሆን አያልፏትም። በዚህች ቀን ምን ተፈጠረ?
ጊዜው ከሰባት አመታት በፊት ነው፣ መስከረም 23፣2006 ዓ.ም ከሊቢያ የተነሳች ጀልባ በጣልያኗ ደሴት ላምፔዱሳ ሰመጠች፤ ጥም ረሃብና መራቆት ሳይበግራቸው፣ ቀያቸውን ለቀው፣ ባህር ተሻግረው የተሻለ ህይወት እናገኛለን ብለውም የተሳፈሩም 366 ስደተኞችም ሞቱ። በወጡበት ቀሩ።
ዮሴፍና አድሃኖም በተአምር ከተረፉት ስደተኞች መካከል ናቸው።
ዮሴፍና አድሃኖም ሞትን ተሻግረዋታል፤ ሃዘንን በጥልቀት ያውቁታል፤ ማጣትንም እንዲሁ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ አብረዋቸው የተጓዙ ስደተኞችን በአሰቃቂ ሁኔታ ከአጠገባቸው ተነጥቀዋል።
ጓደኝነታቸውም የሚጀምረው ከስደት ነው።
የተወለዱበትን ቀዬ ለቆ፣ ባህልና አኗኗር ዘዬ፣ ዘመድና ቤተሰብ ትቶ መሰደድ ምን አይነት ስሜት ይኖረው ይሆን? ዮሴፍና አድሃኖም ይህንን በቅርበት ያውቁታል።
አገራቸው በጦርነት ፈራርሶ፣ ቤታቸው በጦርነት ወድሞ፣ በፖለቲካ እምነታቸው ተሳዳጅ ሆነው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ነገን በማለም የነጎዱትን ታሪክ ይቁጠራቸው። ሃብቴን፣ ንብረቴን፣ ጨርቄንና ማቄን ሳይሉ ብዙዎች ተሰደዋል፤ ሜዳ ላይ ቀርተዋል፣ ጥሙ ረሃቡና መራቆቱ ሳይበግራቸው ባሕርና ተራሮችን ሲያቆራርጡ፤ ባሕር በልቷቸዋል አልያም እንደወጡ ላይመለሱ የቀሩትም በርካቶች ናቸው።
ዮሴፍና አድሃኖም ስደትን የጀመሩት ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ በመሻገር ከዚያም በሱዳን አድርገው ወደ ሰሃራ በረሃ አቀኑ። አጥንት ያቀልጥ በሚመስልና መፈጠርን በሚያስጠላ የሰሃራ በረሃም ላይ አንዲት አንሶላ ለሁለት ለብሰው፤ ተስፋቸውን ሰንቀው ነበር ወደ ሊብያዋ ትራብሎስ ከተማ የገቡት።
የሰሃራን ምድር አቆራርጦ ትራብሎስ ከተማ የገባ ስደተኛ ተስፈኛ ነው፤ ወደ አውሮፓ "የተስፋይቱ ምድር" ለመድረስ፤ የሁለት ሌሊት የባህር ጉዞ ብቻ ነው የሚቀረው።
ሁለት ቀንም ብትሆን ፤ ፀሎትና እድል ካልታከለበት በባህር የተበሉትን ቤቱ ይቁጠረው። ጀልባዋም እስክትሞላ ድረስ መዝርዓ እየተባለ በሚጠራ የባህርዳር መንደሮች ተሰባስበው ነበር።
ዋዜማው ላይም በርካቶች በተስፋና በጭንቀት ተሞልተው ነበር። በርከት ያለ ተሳፋሪ ከተሰባሰበ በኋላ ያቺ ተለቅ ያለች ጀልባ ወደ ባህር ዳርቻው እየተጠጋች መጣች። የሊብያ የባህር ጥበቃዎች እንዳያገኙዋቸው፤ በቲዮታ መኪና እያስጠጉ ነበር የሚያሳፍሩዋቸው።
በፈታኙ የስደት ጉዞ ያልተለያዩት ዮሴፍና አድሓኖም ወደ ጀልባዋ አንድ ላይ ነበር የወጡት።

የፎቶው ባለመብት, YOSEPH AND ADHANOM
ጀልባዋ ከአፍ እስከ ገደፏ በርካታ ሰዎች ጭና ትንሽ ከተንቀሳቀሰች ብኋላ ካፕቴኑ ደላሎችን ጠርቶ መርከቧ ሚዛን ስለሳተች የተወሰኑትን እንዲቀንሱ ጠየቋቸው።
ደላሎቹም ባልተወለደ አንጀታቸው በዱላ እየቀጠቀጡና እየገረፉ 26 ሰዎች አውርደው በትናንሽ ጀልቦች መለሷቸው። ጨለማ ሰለነበር ኣድሓኖም የበረሃ ጓደኛው ዮሴፍ ከተመለሱት መካከል መሆኑን አላወቀም ነበር።
ያቺ ሰዓት
በጀልባዋ ተጭነው የነበሩት 518 ስደተኞች መጨረሻ ከሌለው ባህር ወጥተው በርቀት የደሴቷን መብራቶች ሲያዩ የስቃያቸው መጨረሻ፣ የአዲስ ህይወት ምዕራፍ መስሏቸው ነበር።
በርካቶቹ እዚህ ለመድረስ የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የቤተሰቦቻቸውን ጥሪት አሟጠዋል። ከሊቢያ ብቻ ወደ ጣልያን ለመሻገር እያንዳንዳቸው 1 ሺህ 600 ዶላር ከፍለዋል። ከሰላሳ ስድስት ሰዓታት የማያቋርጥ የውሃ ጉዞ፣ የጋዝ ሽታ በኋላ መሬቱን በርቀት ሲያዩም የአውሮፓ መሬትን ሲመለከቱ በተወሰነ መልኩ የቅዠታቸው መጨረሻም መስሏቸውም ለመውረድ ዝግጅት የጀመሩም ነበሩ።
ካፕቴኑ የጀልባዋ ሞተሩን አጥፍቶ የጣልያን ባህር ጥበቃዎች ገፍተው እንዲያስገቧቸው እየተጠባበቁ ነበር።
በጀልባዋ በላይኛው ክፍል ላይ የነበሩት ብርድ ልብሳቸውን ለብሰው ተቀምጠው የነበረ ሲሆን የተወሰነም ንፋስ ነበረው።
የታችኛው ተጨናንቋል፤ የባህሩ ሽታ እያጥወለወላቸው በርካቶችም ታጉረዋል። በዚህም ወቅት ነው የባህሩ ውሃ ወደ ጀልባዋ መግባት የጀመረው።
በወቅቱ የነበሩ የአይን እማኞችም እንደሚናገሩት ካፕቴኑ ከላይኛው የጀልባ ክፍል ወደታችኛው ወርዶ ሞተሩን ሊያስነሳ ቢሞክርም እምቢ አለው።
የተጨናነቀው ካፕቴን ጋዝ ብርድ ልብስ ላይ አርከፍክፎ ባህር ዳርቻው ላይ በማሳየትም አትኩሮት ለመሳብ ሞከረ። ጀልባም አጠገባቸው መጥቶ እንዲረዳቸውም ለማድረግ ነበር።
ሆኖም ያ ከመሆኑ በፊት እሳቱ እጁን ስላቃጠለው ጣለው። እሳት ጀልባው ላይ መንደድ ጀመረ። ተኝተው የነበሩ ስደተኞች በጩኸትና በእሳቱ በድንጋጤ ተነሱ። በስደተኞች የታጨቀችው በረብሻ፣ በጩኸትና በዋይታ ተሞላች።
በርካቶች ከእሳቱ ለማምለጥም ሲሞክሩና ሲረጋገጡ ጀልባዋም እያጋደለች መስመጥ ጀመረች። ታችኛው የጀልባ ክፍል የነበሩትም የመትረፍ እድሉም አልነበራቸውም።
ከላይ የነበሩት ደግሞ ወደ ባህሩ ተወረወሩ፤ የተወሰኑት በደመነፍስ ጀልባዋን የሙጥኝ ብለው ለመትረፍ ሞከሩ።

የፎቶው ባለመብት, YOSEPH AND ADHANOM
ማን ያውራ የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ በሌሊት፣ በባዕድ አገር ለሰዓታት በህይወት ለመቆየት ታገሉ። ከሰዓታት በኋላም ነው ጥዋት አስራ ሁለት ሰዓት ላይ አሳ ለማጥመድ የወጡ ሰዎች ያዩዋቸው።
የሞቱት ሞተው፤ ያሉት ደግሞ በህይወትና በሞት መካከል እጃቸውን እያውለበለቡ፤ ውሃውን እየተናነቁ በድካምና በተስፋ መቁረጥ መካከል ነበሩ።
በኋላም የባህር ጠባቂዎች መጥተው የተወሰኑትን ለማዳን ሞከሩ። በጀልባዋ የነበሩት ከአስራ ሁለት አመት በታች ህፃናት አልተረፉም።
አለምን ባስደነገጠው በዚህ አደጋም ተቃቅፈው የተገኙ አስከሬኖችም ነበሩ ተብሏል። መለየት የተቻለውንም፣ ያልተቻለውንም፤ አስከሬናቸው የተገኘው ሲሲሊ አካባቢ በሚገኝ መካነ መቃብር አረፉ፤ አፈሩ ይቅለላቸውና።
አድሓኖም ወደ ባህር ከተወረወሩትና ዋኝተው በህይወት ከተረፉት 155 ሰዎች አንዱ ነው።
"እንዴት እንደወጣሁ አሁንም ድረስ ይገርመኛል። በርካታ ዋና የሚችሉ ሰዎች ሞተዋል። እንደ እኔ ዓይነት ምንም የዋና ችሎታ የሌለን ደግሞ በእግዚሄር ፍቃድ በህይወት ተርፈናል።" ይህች ዕለት ለህይወት ሁለተኛ እድል ያገኘባት ዳግም የተወለደባት ቀን አድርጎ ያከብራታል።
አድሃኖም በህይወት ከተረፈም በኋላ ሲያስጨንቀው የነበረው የጓደኛው ጉዳይ ነበር። በተአምር ከሞት የተሻገረው አድሓኖም ዮሴፍ ከመነሻው ደብደብው እንዲወርዱ ከተገደዱት መካከል መሆኑን ስላላወቀ ከባህር የወጡትን ሬሳዎች መካከል ያፈላልግ ጀመር። ሆኖም አልሰመረለትም፤ ሊያገኘው አልቻለም።
አለምን ያስደነገጠውን ይህንን ዜና ሚዲያዎች ሲቀባበሉት ዮሴፍ ሰምቶ ኃዘኑ ጠነከረ፤ ላጣቸው ወዳጆቹ እንባውን አፈሰሰ።
ከመካከላቸው ጥቂት በህይወት የተረፉ መኖራቸውን ሲሰማ ደግሞ ምናልባት ጓደኞቹ በህይወት ተርፈው ይሆን የሚልም የተስፋ ጭንላንጭል ትታየው ነበር።
አድሃኖም በህይወት ከተረፉት መካከል መሆኑን ዮሴፍ ሰማ። ደስታውን መቆጣጠር አቅቶት፤ እምባ ብቻ ነበር የገለፀለት።
በመጨረሻም በስልክ ተገናኙ። ሊቆጣጠሩት በማይችሉት እንባ ታጅበው እንኳን ተረፍክ ተባባሉ፤ ተላቀሱ፤ ምስጋናቸውንም አቀረቡ።
አደጋው ካጋጠመ ከሁለት ወር በኋላ ዮሴፍም አውሮፓ ለመግባት ቆርጦ በሌላ ጀልባ ተሳፈረ።
ዕድለኛ ሆኖም ወደ ጣልያን አገር በሰላም ገብቶ ከአድሓኖም ጋር ለመገናኘት በቁ። የሆነውን ሁሉ በአካል አወሩ።
ሁለቱም ብዙ ሳይቆዩ ጉዟቸውን ወደ ሌላ አውሮፓዊቷ አገር ስዊድን አደረጉ። የጥገኝነት ጥያቄያቸውም ተቀባይነት አገኘላቸው።
ሆኖም መስከረም 23 በየዓመቱ የላምፑዴሳ አደጋ ወደደረሰባት ቦታ ያቀናሉ። ተመሳሳይ አደጋ እንዳይደርስ ግንዛቤ ያስጨብጣሉ።
በዘንድሮውም፣ በአደጋውም ሰባተኛ አመት ወደ ሲሲሊ ተጉዘዋል። "ትዝታው ፊቴ ላይ ድቅን ይልብኛል። በወቅቱ የነበረውን ለቅሶና ዋይታ፣ የሰዎቹ መልክና ሬሳቸው ባህር ላይ ሲንሳፈፍ ማየት፣ማስታወስ ከባድ ነው" በማለትም ከዚህ በላይ ማውራት ባለመቻልም በዝምታ ተዋጠ።
ከአሟሟታቸውና ከትዝታቸው በላይ ደግሞ እንቅልፍ የነሳው ነገር በርካቶች ቤተሰቦቻቸውን ባለመቅበራቸው ሃዘኑ እንዳልወጣላቸው ሲያስበው ነው።
ባለፈው ዓመት ወደ ኢትዮጵያ በመጣበት አጋጣሚም ልጇ በዚህ አደጋ የሞተባት እናት ዛሬም ድረስ ልጇ በህይወት ይኖራል ብላ እንደምታስብ ነገረችው። በርካታ ልጆቻቸውን ለመቅበር እንኳን ያልታደሉ እናቶች ስቃይና መከራ መስማት የሚዘገንንም ሆነበት።
በዚህ አመት ግን ዮሴፍና አድሐኖም በቁጥር የተወከለውን መቃብር እየለዩ የትኛው መቃብር የማን እንደሆን በመለየት እናቶችና ቤተሰቦች አንድቀን ቦታው ድረስ ሂደው ሃዘናቸውን እንዲወጣላቸው እያመቻቹ ይገኛሉ።
በእርግጥ ስራው ቀላል አልሆነላቸውም፤ የትኛው መቃብር የማን እንደሆነ ለመለየት ፈታኝ ሆኖባቸዋል። ሁኔታውም ልባቸውን ነው የሰበረው። ። ለዚህ ጉዳይ የሚቆረቆር መንግሥት ባለመኖሩ በባህሉ መሰረት አፅማቸው ወደ አገርቤት መጥተው የሚቀበሩበት ሁኔታ የኤርትራ መንግሥት ባይፈቅድም ሌሎች በስደተኞች ጉዳይ ላይ የሚሰሩት ድርጅቶች ቢተባበሩ ጥሪ አድርገዋል።
ለዚህ ዓላማ ሲንቀሳቀሱ ድጋፍ ላደረጉላቸው ለኣባ ሙሴ ዘርኣ፣ ኣቦ መንበር ትረ-ኦቶብረ ታረቀ እና ለሌሎች በሟቾች ስም ምስጋናቸውን አድርሷል።
በርካቶቹ ስደተኞች የሰሃራን በረሃ አቆራርጠው አደገኛ በሚባል ሁኔታ ሊቢያ ይደርሳሉ፤ ከዚያም የሜዲትራንያን ባህርንም ተሻግረው አውሮፓ ይገባሉ። በርካቶቹ ድንበር ለማቋረጥ በአዘዋዋሪዎች እጅ ድብደባን፣ መደፈርንና ሌሎች ጥቃቶች ይደርስባቸዋል። አንዳንዶችም በአዘዋዋሪዎች ታግተው በርካታ ሺህ ብሮችን ክፈሉም ተብለው፤ ቤተሰብ፣ ጥሪታቸውን አሟጠው ከፍለዋል።












