ፕሬዚዳንት ኢሳያስ 'በሰብዓዊነት ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች' በስዊድን ክስ ቀረበባቸው

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS

ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን (አርኤስኤፍ) የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በሰብዓዊነት ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ክሱን ስዊድን ለሚገኘው አቃቤ ህግ አቅርቧል።

ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ በተጨማሪ ሰባት ከፍተኛ ባለስልጣናትንም በሰብዓዊነት ላይ በሚፈፀሙ አለም አቀፍ ወንጀሎች ቡድኑ ወንጅሏቸዋል።

ለዚህም እንደ መነሻ የሆነው ለሁለት አስርት አመታት በእስር ላይ የሚገኘው ኤርትራዊ-ስዊድናዊ ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ ጋር በተያያዘ ነው።

ባለስልጣናቱ ጠንከር ያለ ምርመራ እንዲከፈትባቸው፣ ጋዜጠኛውን በማገት፣ በማንገላታትና ያለበትንም ደብዛ በማጥፋት ክስ ይመሰርትባቸዋል ብሎም እንደሚያንም ቡድኑ በድረ-ገፁ አስፍሯል።

በአለም ላይ ለረዥም አመታት በእስር ላይ የሚገኝ ጋዜጠኛ እንደሆነም ቡድኑ በድረገፁ አስፍሯል።

ቡድኑን በመወከል ክሱን ያቀረቡት ሁለት ስዊድናዊ ጠበቆች ሲሆኑ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ፣ የውጭ ጉዳይ፣ የፍትህና የማስታወቂያ ሚኒስትሮችና ሌሎች አራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ተካትተውበታል።

"ባለስልጣናቱ ምንም እንኳን ደረጃቸው ከፍ ያለ ቢሆንም ዳዊትን ይስሃቅን አስረው ለሃያ አመታት እንዲበሰብስ ያደረጉት ግለሰቦች ለወንጀላቸው ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል" በማለት በክሱ ላይ ፊርማቸውን ካስቀመጡት አንዱ የሆኑት

ጠበቃና የኖቤል የሰላም አሸናፊ ሽሪን ኢባዲ ናቸው

ስዊድናዊ ኤርትራዊ ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ

የፎቶው ባለመብት, ©EU/Belga/SCANPIX/KALLE AHLS

የምስሉ መግለጫ, ስዊድናዊ ኤርትራዊ ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ

"እነዚህ ግለሰቦች በፍፁም ማን አለብኝነት የፈለጉትን እንዲያደርጉና መክሰስ የሚችሉም አገራት ከተዋቸው ፍትህ በኤርትራ ሊሰፍን አይችልም" ብለዋል ጠበቃው

ጋዜጠኛና ገጣሚው ዳዊት ይስሃቅ ነፃ ኤርትራን አገለግላሁ በማለት ወደ ትውልድ አገሩ ተመልሶም የለውጥ ደጋፊ የሆነ ጋዜጣም አቋቁሞም ነበር።

ኤርትራም የግል ጋዜጦችን ዘጋች እንዲሁም የሚቀርቡበትን ትችት ዝም ለማሰኘት የኤርትራ መንግሥት በጀመረው ዘመቻም ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችንና ተማሪዎችን ለእስር ዳርጓል።

ዳዊትን ጨምሮ በርካታ የግል ጋዜጣ አዘጋጆችም በጎሮጎሳውያኑ 2001 ለእስር ተዳረጉ።

ጋዜጠኛው ቤተሰቡን፣ ጠበቃውን እንዲሁም በተደጋጋሚ ከተባበሩት መንግሥታትም ሆነ የስዊድን ተወካዮች እንዲያገኙት ጥያቄ ቢቀርብም ማንም ጎብኝቶት አያውቅም።

በህይወት እንዳለ የተጠረጠረው በጎሮጎሳውያኑ 2005 ሲሆን በእስር ላይ በፈታኝ ሁኔታ እንደሚገኝም የቡድኑ ድረ-ገፅ ጠቁሟል።