ኮሮናቫይረስ፡ በኤርትራ ቢራ በኩፖን መሸጥ ተጀመረ

አስመራ ቢራ

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታት ምግብ ቤቶች፣ ካፌዎችና መጠጥ ቤቶቿን በዘጋችው ኤርትራ ቢራ በኩፖን (መሸመቻ ካርድ) መሸጥ መጀመሯ ተገልጿል።

ብቸኛው ሜሎቲ ቢራ በሱቆች በመሸመቻ ካርድ አማካኝነት እየተሸጠ እንደሚገኝም ቢቢሲ ትግርኛ ከምንጮች ያገኘው መረጃ አመላክቷል።

ደንበኞች ቢራውን ማግኘት የሚችሉት በሱቆች ብቻ ሲሆን አንድ ቢራም በአስር ናቅፋ (ወደ 25 ብር በሚጠጋ) ዋጋ እንደሚሸጥ ተገልጿል።

ኩፖኑን (የመሸመቻ ካርዱን) የያዙ ሰዎችም በአንድ ሳምንት መግዛት የሚፈቀድላቸው የቢራ ብዛት ስምንት ጠርሙስ ብቻ ነው።

በኤርትራ ዳቦ፣ ዘይት፣ ስኳርና ማሽላ የመሳሰሉትን መሰረታዊ ሸቀጦች በስርጭት (በመሸመቻ) ካርድ በቀበሌዎች ሲሆን መግዛት የሚቻለው፤ መጠኑም በቤተሰብ ቁጥሩ ይወሰናል።

በተለይም ዳቦ ለመግዛት በአቅራቢያቸው በሚገኙ ዳቦ ቤቶች ተመዝግበውም በየእለቱ ጧት የቤተሰባቸውን ቁጥር መሰረት ባደረገ መልኩም እንዲገዙ ይፈቅድላቸዋል።

ሜሎቲ ቢራም በተመሳሳይ መልኩ እንደ ዳቦና ስኳር በሱቆች በመሸመቻ ካርድ መሸጡ አንዳንድ የመጠጥ ቤት ባለቤቶችን ቅር አሰኝቷል።

በአስመራ የሚገኝ ስሜ አይጠቀስ ያለ አንድ የመጠጥ ቤት ባለቤት ነጋዴ "የንግድ ፍቃድ ያለን ሰዎች ንግድ ቤታችሁን ዝጉ ተብለን፤ ለሰራተኞች ደሞዝ ክፈሉ ተብለን ስናበቃ እኛ ልንሸጠው የሚገባ ቢራ በሱቆች እየተሸጠ ይገኛል" በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል።

ነጋዴው እንደሚለው መጠጥ ቤቶቹ የተዘጉት የሰዎችን መሰባሰብ ለመቀነስ መሆኑን ቢረዳም ቢራው በሱቆች መሸጥ ለመጀመሩ ምክንያቱ ግልፅ አልሆነለትም።

መጠጥ ቤቶቹ ሱቆች አሁን እያደረጉት እንዳለው ቢራ መሸጥ ይችሉም እንደነበር ይናገራል።

"ሰባት ወር ሙሉ ከስራ ውጪ ሆነናል። ለሰራተኞቻችን ደግሞ ምንም ሳንሰራ ደመወዝ እንድንከፍል እየተገደድን ነው። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ደንበኞች ቢራ በሱቆች ገዝተው እየሄዱ ነው፤ ገበያችንንም እያሳጡን ነው" ይላል።

በአሁኑ ወቅት ቢራ በሱቆች መሸጥ ከመጀመሩም ጋር ተያይዞ ወጣቶች በሱቆች ገዝተው ተሰባስበው እየጠጡ እንደሚያመሹም ምንጫችን ትዝብቱን ይገልጻል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሳልፋ የነበረችው ኤርትራ አዋጇን ቀስ በቀስ እያላላች ትገኛለች።

ሰዎችም ከቦታ ወደ ቦታ እንደልባቸው እየተንቀሳቀሱም ይገኛሉ።

በተለይም በአገሪቷ ከጥቂት ከጎረቤት አገራት የመጡ ሰዎች በስተቀር ይህ ነው በማይባል ሁኔታ ወረረሽኙ አለመኖሩ እንዲሁም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ባለመኖራቸው አዋጁ ለምን በይፋ እንደማይነሳ በርካቶች ይጠይቃሉ።

በኤርትራ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ጊዜ ጀምሮ የንግድ እንቅስቃሴ የቆመ ሲሆን በተለይ ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን ህዝብ ከመንግሥት ምንም ዓይነት ድጋፍ ስለማይደረግለት ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ በሆነና በፈታኝ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ምንጮቻችን ይናገራሉ።

"ሜሎቲ" ወይም አሥመራ ቢራ

በኤርትራ አንድ ብቻ የሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። አንድ አይነት ቢራ፣ አንድ አውሮፕላን፣ አንድ ሥርዓት ያለው የባንክ አገልግሎት፣ እንድ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ፣ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ፣ አንድ የቴሌቪዝን ጣቢያ . . .

ከ1939 ጀምሮ በኤርትራ ሲጠመቅ ቆይቷል። ይህ ለኤርትራ ብቸኛ የሆነው ቢራ በበርካቶች ዘንድ ትዝታ እና ተወዳጅነትን ያተረፈ ነው።

የቢራ ፈላጊውን እና የአቅርቦት መጠኑ ተመጣጣኝ ስላልነበረ ከቅርብ ዓመታት በፊት አንድ ሰው ሁለት ቢራ ብቻ ገዝቶ እንዲጠጣ ነበር የሚፈቀድለት።

ከሁለት በላይ ደጋግሞ መጠጣት የፈለገ፤ ቢራ የማይጠጣ ሰው ወደ መጠጥ ቤት ይዞ በመሄድ የዚያን ሰው ኮታ ይጠጣ እንደነበር ሰምተናል። አሁን ላይ በቢራ ፋብሪካው በተካሄደ ለውጥ የቢራ አቅርቦቱን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል።

ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስኑ የድንበር በሮች በተከፈቱ ጊዜ የኢትዮጵያ ቢራ ምርቶች አሥመራን አጥለቅልቀዋት እንደነበረ በዚህም የአንድ ሜሎቲ ቢራ ዋጋ ከ25 ናቅፋ ከ11-15 እንደወረደ ነዋሪዎች ነግረውናል።