ሱዳን ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ለማደስ ስምምነት ላይ መድረሷ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሱዳን ከእስራኤል ጋር በሚኖራት ግንኙነት ዙሪያ ስምምነት ላይ መደረሱን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታውቀዋል። ሱዳንም ከእስራኤል ጋር ግንኙነቷን ያደሰች ሌላኛዋ የአረብ ሊግ አባል አገር ሆናለች።
ሱዳን ከሶስት አስርት አመታት በላይ የገዙዋት ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ከስልጣን መወገድ ተከትሎ የአሜሪካና የሱዳን ግንኙነት መሻሻሉም እየተናገረ ነው።
ሱዳን ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ደፋ ቀና ስትል የነበረው ከአሜሪካ አሸባሪነትን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውስጥ እንድትሰርዛት ለማድረግ እንደሆነ በርካቶች ሲገልጹ ቆይተው ነበር።
እአአ 1948 ላይ እስራኤል እንደ አገር እራሷን ካወጀች ወዲህ ሱዳን ከአገሪቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ወስና ነበር።
ከሰሞኑ ደግሞ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ እና ባህሬንም ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ግንኙነት በተመለከተ ስምምነት ላይ መድረሳቸው የሚታወስ ነው።
በተመሳሳይ እስራኤልና ባህሬን ግንኙነታቸውን ሙሉ በሙሉ ለማሻሻል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ይፋ ያደረጉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ነበሩ።
በወቅቱ "ሁለተኛዋ የአረብ አገር ከእስራኤል አገር የሰላም ስምምነት ላይ ትደርሳለች።" ሲሉ ትዊተር ገፋቸው ላይ አስፍረው ነበር።
ለበርካታ አስርታት በርካታ የአረብ አገራት እስራኤልን የፍልስጥኤም ጉዳይ ከተፈታ በኋላ ግንኙነታቸውን እንደሚቀጥሉ በመግለጽ አግልለው ነበር።
ነገር ግን ባለፈው ወር የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ስምንት ላይ ደርሳለች።
በእስራኤል እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መካከል ያለው ግንኙነት የተለሳለሰው በአሜሪካ አሸማግይነት ሲሆን፤ ነሐሴ 13 ነበር ወዳጅነታቸውን ይፋ ያደረጉት።
በአብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ይህ ዜና በመልካም ቢወሰድም፤ ፍልስጥኤም ግን ተቃውሞዋን ገልጻለች።
በተለይም የአረብ ኤምሬትስ ለፍልስጥኤም እውቅና ካልሰጠችው እስራኤል ጋር ግንኙነት መፍጠራቸው፤ ፍልስጥኤምን መክዳት ነው ተብሏል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጋር ዳግመኛ መወዳጀታቸውን አስታከው በወረራ የተያዘውን ዌስት ባንክ በግዳጅ የእስራኤል ይዞታ የማድረግ እቅዳቸውን ለማዘግየት ተስማምተዋል።
ጆርዳን ደግሞ በአውሮፓውያኑ 1994 ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት የፈረመች ሲሆን ግብጽ ደግሞ 1979 ላይ ከስምምነት መድረሷ የሚታወስ ነው።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ሱዳንን አሸባሪነትን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውስጥ ካስወጡ በኋላ ጋዜጠኞች ወደ ዋይት ሀውስ ክቡ ክፍል እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ ፕሬዝዳንቱ በስልክ ከሱዳን እና እስራኤል መሪዎች ጋር አውርተዋል።
የፕሬዝዳንቱ ረዳት ጁድ ዴር በሁለቱ አገራት መካከል ስምምነት መፍጠር በመካካለኛው ምስራቅ ሰላምን ለማጠናከርና ቀጠናውን ለማረጋጋት ትልቅ ቦታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ አገራቸው አሸባሪነትን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውስጥ መሰረዟን በማስመለከት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን አመስግነዋል።
በስልክ በነበራቸው ቆይታ የእስራኤሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ '' የሰላምን ግዛት እያሰፋን በመሆኑ ደስተኞች ነን፤ ለዚህ ስኬት ለነበሮት ውጤታማ አመራርም ምስጋና ይገባዎታል'' ብለዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ''ገና ከዚህ በኋላም በርካታ ስምምነቶች ይመጣሉ'' ሲሉ ተደምጠዋል።
ነገር ግን የፍልስጤም ነጻ አውጭ ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊው ዋሴል አቡ የዑሱፍ እስራኤል ከሱዳን ጋር የደረሰችው ስምምነት ፍልስጤማውያንን በጀርባ በኩል በስለት እንደመውጋት ነው ብለዋል።












