ትምህርት ፡ ያጠናበትን "አጠሬራ" እየሸጠ ሀብታም የሆነው ወጣት

የፎቶው ባለመብት, Eugene Cheow
"ስኬታማ ቢዝነስ ነው የጀመርኩት፤ ቢዝነሱ ያጠናሁባቸውን ማስታወሻዎች መሸጥ ነው።"
እንዴት አንድ ተማሪ ያጠናባቸውን ማስታወሻዎች በመሸጥ ሺህ ዶላሮችን ሊያገኝ ይችላል?
ዩጌን ቺዎ ይባላል።
ይህ ጥያቄ ፈገግ ያሰኘዋል። "ከፈለኩ አንድ ሙሉ የትምህርት ዓይነት በአጠሬራ ላስቀምጠው እችላለሁ" ይላል፤ በነገሩ ሲቀልድ።
ቺዎ ገና 24 ዓመቱ ነው። በሲንጋፖር የሥነ አስተዳደር ትምህርት ቤት የቢዝነስ ተማሪ ነው።
ለቢቢሲ ስለ ሕይወቱ፣ ስለ ትምህርቱ እና ስለ ስኬታማነቱ አጋርቷል።
በሲንጋፖር የተመሰከረለት የሪልስቴት አሻሻጭ ለመሆን ዩኒቨርስቲ ገብቶ መመረቅ ግድ ይላል። ከዚያ ደግሞ ተከታታይ ፈተናዎችን ማለፍ የግድ ነው።
እሱ ይህን አሳክቷል። ቺዎ አላማውን ካሳካ በኋላ ነው ተፈትኖ ያለፈባቸውን የጥናት ካርዶች (በእኛ ዩኒቨርስቲዎች በተለምዶ አጠሬራ የሚባሉትን) በበይነ መረብ ለገበያ ያቀረበው።
ይህንን ነገር ለመሞከር ቺዎ የመጀመርያው ሰው አይደለም። ነገር ግን የእሱ የጥናት ካርዶች በጣም ስኬታማ ሆነዋል።
እስካሁን 1,500 የጥናት ካርዶችን ሽጧል። በሳምንት እስከ 1ሺህ ዶላር ወደ ኪሱ ያስገባል። ቀስ በቀስ ነገሩን ወደ ቢዝነስ አሳድጎታል።
ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በሲንጋፖር የሪልስቴት እውቅና ያለው አሻሻጭ ለመሆን 60 ሰዓት የሚወስድ ኮርስ ማጠናቀቅ ያሻል። ከዚያ ሁለት ክፍል ያለው አር-ኢ-ኤስ የሚባል ፈተና መውሰድ የግድ ነው።
"ፈተናውን ማለፍ ቀልድ አይደለም። እንደሚታወቂው በሲንጋፖር መመሪያዎች ጥብቅ ናቸው" ይላል ለቢቢሲ።
ይህን ቢዝነስ ለመጀመር እንዴት ሐሳቡ እንደተከሰተለት ሲናገርም፤ "ሰዎች በቀላሉ በአቋራጭ አንድን ነገር መረዳት ይፈልጋሉ፤ ለዚህ ደግሞ ቀላልና አጭሩ መንገድ የጥናት ካርዶች እንደሆኑ ገባኝ" ይላል።
ደንበኞች አንድ ጊዜ ክፍያ ፈጸመው 16 የጥናት ካርዶችን ወደ ስልካቸው ወይም ወደ ኮምፒውተራቸው መጫን ይችላሉ። እነዚህ ፈተናውን ለማለፍ በቂ የሚባሉ ናቸው።
እነዚህ የጥናት ካርዶች ግን ተራ የጥናት ካርድ አይደሉም። ማይንድ ማፒንግ በሚባል የማስታወስ ሥነ ዘዴ የተቀኙ ናቸው። ውስብስብ ሐሳቦችን በቀላሉ በግራፍና በምሥል ማስታወስ እንዲቻል የሚያግዙ ናቸው። ቁልፍ ቃላትን በመያዝ አንድን ሙሉ ሐሳብ ወደ አእምሮ አምጥቶ መያዝን ያስችላሉ።
ዋናው የማንይድ ማፒንግ ማስታወሻ ካርዶች ጥቅም አንድን ውስብስብ ሐሳብ በምሥል መወከል ነው። አንድ ምሥል ወይም ቃል አንድ ምዕራፍን ሊወክል ይችላል።
የቺዎ ካርዶች የሕግ ሐሳቦችን፣ የማርኬቲንግና የሒሳብ ቀመሮችን፣ ሰንጠረዦችን ወዘተ የያዙ ናቸው።
አንድ ተማሪ አንድን ጽንሰ ሐሳብ ከትምህርቱ ቢዘነጋ ወፋፍራም መጽሐፍትን ተመልሶ ማገላበጥ አያስፈልገውም። አንዲት የአጠሬራ ካርድ ትበቃለች።

"ንግግር የግድ አይደለም"
ቺዎ ንግግር አንድን ሐሳብ ለማስረዳት የግድ እንዳይደለ ይናገራል።
ይህን የተረዳው የባሕር ጠላቂነት ስፖርት ላይ ነው።
አንድ ሰው እየዋኘ ባሕር ውስጥ ከማንም ጋር አይነጋገርም። ሰላታም መለዋወጥ አትችልም። የመጥለቂያ መተንፈሻ ጭምብሌ ተቀዷል ለማለት እንኳ በምልክት ነው።
ከ14 ዓመቱ ጀምሮ የባሕር ጠላቂነትን ተምሯል። ከዚያ በኋላም ሰዎችን ያሰለጥን ነበር። በፊሊፒንስ፣ በኢንዶኒዢያ እንዲሁም በማሌዢያ ይህን አሰልጥኗል።
"ይህ ሁሉ ያስተማረኝ ነገር ንግግር ሐሳብን ለመረዳት የግድ እንዳልሆነ ነው" ይላል።
"የጥናት ካርዶቼም የምልክቶች ስብስቦች ናቸው"
የባሕር ጠላቂነት ስፖርት በትንሹ ሁለት ነገር አስተምሮኛል። አንዱ ከተለያዩ ባሕል የመጡ ሰዎች ጋር መግባባትን ነው። ሁለተኛው ደግሞ የብዙ ቃላትን አላስፈላጊነት።
አሁን ይህን ቢዝነስ ወደ ኮምፒውተሩ ዘርፍ [አይቲ] ለመውሰድ እያሰበ ነው። ምክንያቱም የቢዝነስ ሞዴሉ በአንድ የትምህርት ዓይነት ብቻ ከቆመ ገቢው ቀጣይነትና አስተማማኝ ሊሆን ስለማይችል ነው።
ጥናት ከፍ ማድረግ ይሻል።
"ብዙውን ጊዜ ሥራውን ለነፍሴ ስል ነው የምሰራው። በተለይ ሰዎች የእኔን የጥናት ካርድ (አጠሬራ) ተጠቅመው ከባዱን ፈተና እንዳለፉ ሲነግሩኝ ደስታዬ ወደር ያጣል። ለእኔ ከዚህ በላይ ክፍያ የለም" ይላል።
















