ሕንድ፡ ነፍሰጡር ባለቤቱ ላይ ጥቃት የፈጸመው ግለሰብ ልጁን አጣ

የፎቶው ባለመብት, CHITRANJAN SINGH / BBC
ሕንድ ውስጥ አንዲት ነፍሰጡር ሴት በባለቤቷ አማካይነት ሆዷ ለግብርና በሚውል ስል መሳሪያ በመቀደዱ ህጻኑ ሕይወቱ አልፎ እንዲወለድ ማድረጉን የሕንድ ፖሊስ አስታወቀ።
የእናቲቱ ቤተሰቦች ለፖሊስ እንደገለጹት ባለቤቷ የሚወለደውን ህጻን ጾታ ለመለየት በማለት ጥቃቱን እንደፈጸመባት ገልጸዋል።
አክለውም ጥንዶቹ ከዚህ በፊት አምስት ሴት ልጆች ያፈሩ ሲሆን ባልየው ወንድ ልጅ እንድትሰጠው አጥብቆ ይጨቀጭቃት እንደነበረ አስታውቀዋል።
በአሁኑ ሰአት በቁጥጥር ስር የሚገኘው ግለሰቡ ሆነ ብሎ ባለቤቱ ላይ ጉዳት እንዳላደረስ በመግለጽ የተከራከረ ሲሆን፣ አደጋው የተከሰተው በአጋጣሚው ነው ብሏል።
ይህ ነገር የተከሰተው በሰሜናዊ ሕንድ ከፍተኛ ሕዝብ በሚገኝበት ኡታር ፕራዴሽ ግዛት ሲሆን አካባቢው ደግሞ ባዱአን በመባል ይታወቃል።
የፖሊስ ኃላፊዎች ለቢቢሲ እንደገለጹት ጉዳት የደረሰባት እናት በአሁኑ ሰአት ጤንነቷ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን በዋና ከተማዋ ዴልሂ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ክትትል እየተደረገላት ነው።
ጉዳት የደረሰባት እናት እህት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ስትናገር ጥንዶቹ ወንድ ልጅ መውለድ ባለመቻላቸው ለረጅም ጊዜ ይጨቃጨቁ ነበር ብላለች።
ጉዳት የደረሰባት እናት ጌልሂ ወደሚገኘው ሆስፒታል ትናንት እሁድ ዕለት እንድትዘዋወር የተደረገችው ጤንነቷ በወቅቱ አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ ደርሶ ስለነበረ እንደሆነ የገለጸው ደግሞ ወንድሟ ነው።
ባለቤቷ በበኩሉ ጉዳት ለማድረስ ሆነ ብሎ ያደረገው ነገር እንደሌለ በመግለጽ፣ ለግብርና የሚጠቀምበትን መሳሪያ በንዴት እንደወረወረባት ጠቁሟል። ''ነገር ግን እንዲህ አይነት ጉዳት ይደርስባታል ብዬ በፍጹም አልገመትኩም'' ብሏል ለፖሊስ በሰጠው ቃል።
''አምስት ሴት ልጆች አሉን፤ አሁን ደግሞ ብቸኛው ወንድ ልጄ ሕይወቱ አልፏል። ልጆች የፈጣሪ ስጦታዎች እንደሆኑ አውቃለሁ። መሆን ያለበት ነገር በሙሉ ይሆናል'' ሲልም ተደምጧል።
ፖሊስ ምርመራውን አሁንም ድረስ እያከናወነ እንደሆነ ገልጿል።
ሕንድ ውስጥ ቤተሰቦች ወንድ ልጅ ለማግኘት በጣም የሚፈልጉ ሲሆን አብዛኛዎቻቸውም ከሴት ልጆች ይልቅ ወንድ ልጆች እንዲኖሯቸው ነው የሚፈልጉት።
በሕንድ ባለፉት 50 ዓመታትም 46 ሚሊየን የሚደርሱ ሴት ልጆች የት እንደገቡ የማይታወቅ ሲሆን በየዓመቱ ደግሞ እስከ 460 ሺ የሚደርሱ ሴት አዲስ የሚወለዱ ህጻናት በውርጃ አልያም በተመሳሳይ ጥቃቶች ሕይወታቸው እንደሚያልፍ የተባበሩት መንግሥታት የስነ ህዝብ ፈንድ መረጃ ይጠቁማል።












