የታይላንድ ብሔራዊ ፓርክ ጎብኚዎች የጣሉትን ቆሻሻ በአድራሻቸው ሊልክ ነው

የፎቶው ባለመብት, Facebook/TOPVarawut
ፓርክ ውስጥ ሄደው የበሉትን የምግብና ፍራፍሬ ትርፍራፊ ዝም ብለው የሚጥሉ ከሆነ የታይላንድ ብሔራዊ ፓርክ ትምህርት ያስተምርዎታል።
በፓርኩ ውስጥ ቆሻሻ ከጣሉ ቀደም ብለው በሰጡት አድራሻ መሠረት ፈልጎ ካሉበት ድረስ ይልክልዎታል።
ስለዚህ ዝም ብሎ ቆሻሻ መጣል ቀረ።
በታይላንድ የሚገኝ ታዋቂው ካዎ ናይ ብሔራዊ ፓርክ የጣሉትን ቆሻሻ በጎብኚዎች አድራሻ መልሶ እንደሚልክ የአገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ አካባቢውን በቆሻሻ የበከሉት ሰዎችም በፖሊስ ይመዘገባሉ።
ጎብኚዎች ወደ ፓርኩ ሲገቡ አድራሻቸውን የሚያስመዘግቡ ሲሆን ቆሻሻም ከጣሉ በቀላሉ ፈልጎ ለማግኘትና በሰጡት አድራሻም ለመላክም ያስችላል ተብሏል።
የአገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ቫራውት ሲልፓ አርቻ ቆሻሻዎችን ሰብስበው ፎቶ አንስተው በፌስቡክ ገፃቸው የለጠፉ ሲሆን ቆሻሻውን ለጣለው ሰው ሊላክም ዝግጁ ነው ብለዋል።
"ቆሻሻችሁን እንመልስላችኋለን" ያለው የፌስቡክ ፖስት ቆሻሻ በብሔራዊ ፓርክ መጣል ለአምስት ዓመት እስር እንደሚዳርግ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስቀጣ ወንጀል እንደሆነም አስታውሰዋል።
ባዶ የፕላስቲክ ጠርሙሶች፣ ቆርቆሮዎች፣ የምግብ መጠቅለያ ፕላስቲኮችን በአንድ ካርቶንም ውስጥ ተደርጎ "እነዚህን እቃዎች በካዎ ያይ ብሔራዊ ፓርክ ረስታችኋል" ከሚልም ፅሁፍ ጋርም ነው በፌስቡክ ፖስት የተደረገው።
የፓርኩ ባለስልጣናት እንደሚሉት በፓርኩ የተተውት ቆሻሻዎችን እንስሳቱ ለመብላት እንደሚሞክሩና ለእንስሳቱ ደኅንነትም አደገኛ ናቸው ብለዋል።
ካሃዎ ያይ ብሔራዊ ፓርክ ከታይላንድ መዲና ባንኮክ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኝ ሲሆን 2 ሺህ ሰኩዌር ኪሎሜትር ስፋት አለው። ለተለያዩ እንቅስቃሴዎችና ተራራ በሚወጡ ሰዎችም ተመራጭ ቦታ ነው።
በታይላንድም ውስጥ ጥንታዊ ብሔራዊ ፓርክ ሲሆን በፏፏቴዎቹ፣ ባለው የእንስሳት ብዛትና በቦታው ማማር ይታወቃል።












